''ሕገ መንግሥቱን ለመጠበቅ ወታደራዊ ግዳጅ ለመፈጸም ዝግጁ ነን''- የሰሜን ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ አባላት

108
መቀሌ ሰኔ 23 / 2011 የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትን በመጠበቅ ወታደራዊ ግዳጃቸውን ለመፈጸም ዝግጁ መሆናቸውን በመከላከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ አባላት ገለጹ። ሠራዊቱን በብሔር በመከፋፈል አገሪቱን ለማተራመስ የታሰበው ሴራ እንደማይሳካም ተናግረዋል፡፡ የመምሪያው አባላት ለኢዜአ እንደገለጹት ሠራዊቱ  አንድነቱን አስጠብቆና ሕገ መንግሥዊ ሥርዓቱን አስከብሮ አገራዊ ተልዕኮውን ለመወጣት ዛሬም ዝግጁ ነው። ኮሎኔል ገብረመድህን ተስፋይ በሰጡት አስተያየት የጦር ኃይሎች ኤታ ማዦር ሹም በነበሩት ጄኔራል ሰዓረ መኮንንና ሜጀር ጄኔራል ገዛኢ አበራ ላይ የተፈጸመው ግድያ የሠራዊቱን ታሪክ እንደማያደበዝዘው ተናግረዋል። "ሠራዊቱ በየምዕራፉ መስዋዕትነት እየከፈለ መጥቷል" ያሉት ኮሎኔል ገብረመድህን፣ በዚህም አገሪቱን ከስጋት በመጠበቅ እድገት እንድታስመዘግብ ማድረጉን አስረድተዋል። የሠራዊቱ አባላት ከፍተኛ የጦር መኮንኖች መስዋዕት የሆኑለትን ዓላማ በመረዳት ኢትዮጵያ ወደ ተሻለ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ እንድትደርስ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ እያስከበሩ መሆኑን አመልክተዋል። ሠራዊቱ በብሔርና ሃይማኖትሳይለያይ ለሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መቆሙን የተናገሩት ኮሎኔል ገብረ መድህን፣ ይሄም ሠራዊቱ በጥንካሬው እንዲቀጥል አድርጎታል ብለዋል። ሌላው የሠራዊቱ አባል ኮሎኔል ገብረመስቀል ገብረ ኪዳን ከፍተኛ የጦር መኮንኖቹ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ተጠብቆ እንዲቀጥል ሲሰሩ እንደነበር አስታውሰው፣ሠራዊቱ የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነውን ሕገ መንግሥት ከመጠበቅ አንጻር የሕይወት መስዋዕትነትም ጭምር ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል። ኮሎኔል ክታብ አንሰርሙ በበኩላቸው የጄኔራል መኮንኖች ህልፈት የሠራዊቱን ጊዜ ከባድ ቢያደርገውም፤ በቀላሉ በማይበታተን መልኩ የተደራጀው ሠራዊትን በብሔር ለመከፋፈል ጥረት የሚያደርጉ አካላት እንደማይሳካላቸው ገልጸዋል። ሌላው የሠራዊቱ አባል ሻለቃ አዜብ ተካ በበኩላቸው ተሞክሮ የከሸፈው መፈንቅለ መንግሥት በሕገ መንግሥቱ ላይ የተቃጣ ጥቃት መሆኑን ተናግረዋል። ሠራዊቱ ሕገ መንግሥቱንና የአገር ሉአላዊነት የመጠበቅ ግዳጁን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል። ከፍተኛ የጦር መኮንኖቹ ከአንድ ሳምንት በፊት በጄኔራል ሰዓረ መኮንን ጠባቂ በተተኮሰ ጥይት ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም