የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ 1 ሺህ 313 ተማሪዎችን አስመረቀ

97
ሰኔ 22/2011 የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ፕሮግራም ያስተማራቸውን 1 ሺህ 313 ተማሪዎችን አስመረቀ። ዩኒቨርሲቲው በአምስት ኮሌጆች ውስጥ ያስተማራቸውን ተማሪዎች 1 ሺህ 112 በመጀመሪያ ዲግሪ እና 201 በሁለተኛ ዲግሪ በዛሬው ዕለት አስመርቋል። የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶክተር ታረቀኝ ብርሃኑ በስነ ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፤ ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲው ባገኙት እውቀትና ክህሎት አገራቸውንና ህዝባቸውን በታማኝነት ማገልገል አለባቸው። ''ዩኒቨርሲቲው በሳይንስ፣ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ(አይሲቲ) እና በኢንጅነሪንግ ትምህርት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚያስተምር በመሆኑ ተማሪዎችም በዚሁ መስክ የአገሪቱን ዕድገት ለማፋጠን መስራት ይኖርባቸዋል'' ብለዋል። ዩኒቨርሲቲው ከኢንዱስትሪዎች ጋር ትስስር በመፍጠር ችግር ፈቺ የሆኑ ምርምሮችን እንደሚያካሂድና አጫጭር ስልጠናዎችን በመስጠት ለአገሪቱ ዕድገት የበኩሉን እየተወጣ እንደሆነም ጠቁመዋል። ተመራቂዎች በበኩላቸው ባገኙት እውቀት አገራቸውንና ህዝባቸውን ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል። በኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ ማኔጅመንት ተመራቂ የሆኑ ተማሪዎች ለኢዜአ ሪፖርተር እንደተናገሩት፤ ከዩኒቨርሲቲው ባገኙት ዕውቀትና ክህሎት አገራቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ለመጥቀም ይሰራሉ። ወደ መንግስትም ሆነ ግል ተቋማት በመሄድ በንድፈ-ሐሳብ ደረጃ ያገኙትን ትምህርት በተግባር ማስደገፋቸውን ገልጸው በኮንስትራክሽ ዘርፍ የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል። በተመሳሳይ በኢንዱስትሪያል ኬሚስትሪ የተመረቁ ተማሪዎች ያገኙትን ዕውቀት ለማህበረሰቡ ለማበርከት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም