ያገኘነውን እውቀትና ማህበራዊ መስተጋብር በስራ ለመተግበር ተዘጋጅተናል - ተመራቂ ተማሪዎች

151
ሰኔ 22/2011 በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ያገኙትን እውቀትና ማህበራዊ መስተጋብር በስራ ለመተግበር መዘጋጀታቸውን አስተያየታቸውን የሰጡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎች ተናገሩ፡፡ የተማረበት ሙያ አካላዊ ና ስነ-ልቦዊ ጉዳት ያለባቸውን የህብረተሰብ ከፍል በመቅረጽ ለሀገር እድገት እውቀትን ብቻ ሳይሆን ሰብአዊነትን የሚጠይቅ በመሆኑ የበኩሉን ለማበርከት መዘጋጀቱን የልዩ ፍላጎት ተመራቂው አያልሰው ሙላቴ  ተናግሯል። ዩኒቨርሲቲ የብዙ ሰዎች መገኛ በመሆኑ የባህል፣የቋንቋና ማህበራዊ ትስስር የሚታይበት ነው ያለው አያልሰው፤ በየወቅቱ የሚፈጠሩ ችግሮች የስጋት መነሻ በመሆናቸው ራስን ከዚህ መቆጠብ እንደሚገባ  ተናግሯል፡፡ “ዩኒቨርሲቲ ስንገባ ከጎጠኛ አስተሳሰብ በመውጣት የራሳችን እንዲደመጥ እንደምንፈልገው ሁሉ የሌሎችን ለመቀበል ራሳችንን ክፍት ማድረግ አለብን” በማለት ከዩኒቨርሲቲዎች የሚመጡ ወሬዎችን በማጣራት ራስን መጠበቅ እንደሚገባም ገልጿል፡፡ ”አንድ ሰው የሚውደውን ሙያ መማር አለበት፤ በሙያውም ህዝብን መጥቀም አለበት” የሚለው የህግ ትምህርት ክፍል  ተመራቂ  ዳዊት ታምሩ፤ እሱም ተመርቆ ሲወጣ  የበኩሉን እንደሚያበረክት ጠቅሷል። “ምንም እንኳን የተለያየ ፍላጎት ቢኖረኝም በምስራበት መስክ ጥሩ ውጤት ለማምጣትና ህዝብን በቅንነት ለማገልገል ፍላጎቱ አለኝ” ያለው ዳዊት ፍላጎት ብቻ ሆኖ እንዳይቀር ውጫዊ ተጽእኖ እንዳያሸንፈው ጥረት እንደሚያደርግ ገልጿል። ዩኒቨርሲቲ ብዙዎች እንደሚያስቡት እየተዝናኑ የሚማሩበት ብቻ ሳይሆን ሀላፊነትን የሚማሩበትና ከቤተሰብም ርቆ ራስህን መሚራት የሚቻልበት እንደሆነ መረዳቱንም ነው የተናገረው። የዩኒቨርሲቲ ቆይታ ብዙ ነገሮች በውጫዊ ተጽእኖ ስር መሆናቸው ውጤታማ ለመሆንም ሆነ   ለውድቀት መነሻ በመሆኑ፤ መልካም ጓደኛና ማህበራዊ ግንኙነት መመስረት አስፈላጊ  እንደሆነም ይጠቅሳል። “ብዙዎቹ ልዩነቶች ተፈጥሮአዊ ነገሮች ናቸው፤  አንዳንዶቹም አርተፊሻል ሊሆኑ ይችላሉ” ያለው ተማሪ ዳዊት ልዩነትን ማጥበብ ይገባል ነው ያለው። የማህበረሰብ ጥናት ተመራቂዋ ትዕግስት ማስረሻ በበኩሏ በታችኛው የትምህርት ደረጃ  ተመሳሳይ ባህልና አኗኗር ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ከሰዎች ጋር ለመተዋወቅ አስቸጋሪ የሚመስል መሆኑን ገልጻ፤  የዩኒቨርሲቲ ህይወት ከብዙ ሰዎች ጋር የመገናኘትና አብሮ መኖርን የሚማሩበት መሆኑን ትናገራለች። ይህ በግል ህይወት ለምትመሰርተው ማህበራዊና ቤተሰባዊ ህይወትም መሰረት  ነው ያለችው ትዕግስት፤ “ትምህርት የሚባለው የአስተሳሰብ ለውጥ ሲመጣ ነው፤ ይህ ከሌለ ፊደል ምንም ትርጉም የለውም፤ ከዛውጭ የሆነ ቦታ ተቀጥረን ደሞዝ ለማግኘት ከሆነ ትርጉም የለውም “በማለት ትገልጻለች። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋ ጥናት ተመራቂ ኤልሳ አለሙ እንዳለችው ቀደም ሲል በአማርኛ ትምህርት ውስጥ  ከሚሰጠው የቋንቋ ጥናት እውቀት ባለፈ የጠለቀ እውቀት እንዳልነበራት አስረድታለች፡፡ በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋም ዘርፉ ለሀገር እድገትና ማህበራዊ መስተጋብር ያለውን ፋይዳ በመረዳቷ ባገኘችው እውቀት የበኩሏን ለማበርከት መዘጋጀቷን ተናግራለች፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም