የትራንስፖርት ዘርፉን ለማሻሻል የተዘረጋው ሀገራዊ የተቀናጀ የቁጥጥር ስርአት ውጤታማ መሆኑ ተገለፀ

126
ሰኔ 22/2011 እየተጠናቀቀ ባለው 2011 በጀት ዓመት የተቀናጀ ሀገራዊ የቁጥጥር አሰራር በመዘርጋት ውጤታማ ተግባር ማከናወኑን የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን አስታወቀ። ሀገር አቀፍ የትራንስፖርት ዘርፍ የ2011 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃጸም ግምገማ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል። በባለስልጣኑ የፖሊሲ ጥናትና ፕላኒንግ ዳይሬክተር አቶ ፍሰሃ መብራህቶም በወቅቱ እንደገለፁት ባለስልጣኑ በበጀት ዓመቱ ውስጣዊና ውጫዊ ሁኔታዎችን በመዳሰስና ክፍተቶችን በመለየት ውጤታማ ስራዎችን አከናውኗል። በተለይ የቁጥጥርና የማስፈፀም አቅምን ለማሳደግ አምስት አዳዲስ ህጎች እንዲወጡና የሰባት ነባር ደንቦችና መመሪያዎች እንዲሻሻሉ መደረጉን ለአብነት ጠቅሰዋል ። የትራንስፖርት አዋጅ ቁጥር 468/1997፣ የተሸከርካሪ ክብደትና መጠን  ደንብ፣ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ደንብ፣ የዲሜሬጅአዋጅ ማስፈጸሚያ ደንብ ተሻሽለው ለትራንስፖርት ሚኒስቴር መቅረባቸውን ተናግረዋል ። የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የጥፋተኛ አሽከርካሪዎች የሪከርድ መረጃ አያያዝ መዘርጋቱና የራዳር አጠቃቀም የዓቅም ግንባታ፣ ድጋፍና ክትትል ስራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል። ዳይሬክተሩ እንዳሉት በቴክኖሎጂ የታገዘ የአገልግሎት አሰጣጥ በመዘርጋት ህገ-ወጥነትን ለመከላከል በተደረገ ጥረት ብልሹ አሰራሮች ላይ የማስተካከያ እርምጃዎች ተወስደዋል። የትራንስፖርት ዘርፉ የወጭና ገቢ ምርቶችን በተሳለጠ ሁኔታ በማጓጓዝ የሀገር ኢኮኖሚ በተረጋጋ መልኩ እንዲቆይ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ነው የገለጹት። “የገቢ ማሰባሰብና የካፒታል ፕሮጀክቶች ትግበራ አቅምን በማሻሻል የሀብት አስተዳደር ስርአቱን ውጤታማ ማድረግ ተችሏል” ያሉት ዳይሬክተሩ በአጠቃላይ የባለስልጣኑ የበጀት ዓመቱ የስራ እቅድ አፈጻጸም 87 ነጥብ 8 በመቶ መሆኑን ተናግረዋል። የኦሮሚያ ትራንስፖርት ባለስልጣን ተወካይ አቶ አዱኛ ከበደ በበኩላቸው "በበጀት ዓመቱ በክልሉ ተደራሽና ደህንነቱ የተጠበቀ የትራንስፖርት አገልግሎት ለህብረተሰቡ ለማዳረስ ጥረት ተደርጓል"  ብለዋል፡፡ በመንገድ ደህንነት ህግ ለ617 ሺህ ሰዎች ግንዛቤ ለማስጨበጥ ታቅዶ ለ 4 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሰዎች ትምህርት መሰጠቱን በምሳሌነት ጠቅሰዋል ። የትራንስፖርት አገልግሎት ለማሻሻልና ለመለወጥ በ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ወጪ በአዳማ፣ ሮቤ፣ ሻሸመኔ፣ ጅማና ነቀምቴ የዘመናዊ መናኸሪያ ግንባታ መጀመሩንም አመልክተዋል። “በመንጃ ፍቃድ ህትመት የተስተዋለውን የመልክም አስተዳደር ችግር ለመፍታት ባለስልጣኑ አዲስ የህትመት ማሽን በመግዛት ከ120 ሺህ በላይ የመንጃ ፍቃድ ህትመት እንዲሰራ አድርጓል” ብለዋል። በበጀት ዓመቱ በ946 ሺህ 395 ተሽከርካሪዎች ላይ በተካሄደ የመደበኛ ቁጥጥር ከ52 ሺህ የሚበልጡት ህግን ተላልፈው በመገኘታቸው 6 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር እንዲቀጡ ተደርጓል ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ የእቅድ ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክተር አቶ ስመኘው ይሄኔ ናቸው።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም