የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን በምክንያታዊ አስተሳሰብ በመታገዝ ለውጡን እንዲያስቀጥሉ ጥሪ ቀረበ

50
ሰኔ 22/2011የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን የቀሰሙትን እውቀት ከምክንያታዊ አስተሳሰብ ጋር በማጣመር ለውጡን ለማስቀጠል እንዲሰሩ ጥሪ ቀረበ። የአሶሳና የአክሱም ዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ የትምህርት መርሃ-ግብሮች ያሰለጠኗቸውን 8 ሺህ 116 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቀዋል። በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ በተካሔደው የምረቃ መርሃ-ግብር ላይ የተገኙት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሒሩት ወልደማርያም እንደገለጹት ተመራቂዎች በትምህርት ቆይታቸው ያገኙትን እውቀት ከምክንያታዊ አስተሳሰብ ጋር አጣምረው ለሃገራቸው የሚጠቅም ስራ ሊያከናውኑ ይግባል። ዘንድሮ በመላው ሃገሪቱ ከሚገኙ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች 152 ሺህ 463 ተማሪዎች እንደሚመረቁ የገለጹት ሚኒስትሯ ከድህነት ለመውጣት በክህሎችና በስነ-ምግባር የታነጸ ምሁር አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል። “ሃገራዊ ለውጡ ኢትዮጵያዊያን በህይወት መስዋዕትነት ጭምር ያመጡት ነው” ያሉት ሚኒስትሯ ውጤቱ ደግሞ አንድነቷ የማይናወጥና ዜጎቿ በተደላደለ ሁኔታ የሚያሳልፉባትን ሃገር ለመገንባት መስራት እንደሆነ አስታውቀዋል። የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ተወካይ ዶክተር ኃይማኖት ዲሳሳ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ዛሬ ያስመረቃቸው 2ሺህ 716 ተማሪዎች በ36 የትምህርት ዘርፎች በመደበኛና መደበኛ ባልሆኑ ፕሮግራሞች የሰለጠኑ መሆናቸውን ገልጸዋል። ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ስራው ጎን ለጎን ችግር ፈቺ የሆኑ 12 ማህበረሰብ አቀፍ የምርምር ፕሮጀክቶችን እያካሔደ መሆኑንም አስታውቀዋል። በተመሰሳይም ዜና በአክሱም ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ምረቃ ላይ የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የትግራይ ክልል የከተማ ልማት ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አብርሃም ተከስተ እንደገለጹት ተመራቂዎች የኢትዮጵያን አንድነት ለማስቀጠልና ሰላምን ለማረጋገጥ የመስራት ኃላፊነት አለባቸው። በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ያገኙትን እውቀት በምክንያታዊ አስተሳሰብ በማዳበርም ለሃገር ልማት ሊያውሉት እንደሚገባም አሳስበዋል። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ጸሐዬ አስመላሽ በበኩላቸው ተመራቂዎች የመጪውን ዘመን ኃላፊነት በመሸከም በእውቀትና በራስ በመተማመን ለሃገር ሰላምና እድገት አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። "ሃገሪቱ እየገጠማት ካለው ችግር በመላቀቅ የእድገት ጎዳናዋን እንድታስቀጥል ተመራቂዎች ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው" ብለዋል። በተለይም የመቻቻል የመከባበርና አብሮ የመኖር እሴትን በማስቀጠል ተማሪዎች በሔዱበት ቦታ ሁሉ ሊሰሩ እንደሚገባም ፕሬዝዳንቱ አሳስበዋል። በህግ የመጀመሪያ ዲግሪ ተመራቂ የሆነችው ሩሃማ ሁሴን በዩኒቨርሲቲው ቆይታዋ ያገኘችውን እውቀት ተጠቅማ ወቅቱ የሚፈልገውን የፍትህ አገልግሎት ተደራሽነት ለማሳደግ እንደምትሰራ ተናግራለች። ብሔር ኃይማኖት፣ የፖለቲካ አመለካከትና ማንንት ሳይገድባት በሃቀኝነት ሁሉንም ዜጋ በእኩልነት ለማገልገል መዘጋጀቷንም አስረድታለች። ከ5ሺህ 400 በላይ ከሚሆኑት የአክሱም ዩኒቨርሲቲ የዘንድሮ ተመራቂዎች መካከል ከ130 በላይ የሚሆኑት በሁለተኛ ዲግሪ የሰለጠኑ መሆናቸው ተገልጿል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም