በከሸፈው መፈንቅለ-መንግስት እጃቸው አለበት የተባሉ ቡድኖችና ግለሰቦች ላይ የሚወሰደው ህጋዊ እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል-አዴፓ

58
ሰኔ 22/2011የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) በከሸፈው መፈንቅለ-መንግስት እጃቸው ያለበትን ግለሰቦችና ቡድኖች በህግ ቁጥጥር ስር የማዋልና ህጋዊ እርምጃ የመውሰድ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ። የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ማዕከላዊ ኮሚቴ ሰኔ 21 ቀን 2011 ዓ.ም አስቸኳይ ስብሰባ  አካሂዷል። በስብሰባውም የከሸፈው መፈንቅለ-መንግስት የጥፋት ሴራ መሆኑን ገምግሞ ባለ 6 ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥቷል፡፡ ማዕከላዊ ኮሚቴው አስቸኳይ ስብሰባውን ያካሄደው በብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ፅጌ  አቀነባባሪነት  ተሞክሮ በከሸፈው የመፈንቅለ መንግስት፣ በክልሉ መሪዎች መስዋዕትነት፣ በአገሪቱ የመከላከያ መኮንኖች ጥቃትና ተያያዥ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ነው። ማዕከላዊ ኮሚቴው ባወጣው መግለጫ በከሸፈው መፈንቅለ-መንግስት እጃቸው ያለበትን ግለሰቦችና ቡድኖች በጸጥታ መዋቅሩና በህዝቡ ርብርብ አብዛኞቹን በአጭር ጊዜ በህግ ቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል። ሌሎች በጥቃቱ እጃቸው አለበት የተባሉ ቡድኖችና ግለሰቦችን በህግ ቁጥጥር ስር የማዋልና ህጋዊ እርምጃ  የመውሰድ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ማዕከላዊ ኮሚቴው አስታውቋል። የፀጥታ መዋቅሩን መልሶ ለማጠናከር ሀብረተሰቡን በማስተባበር በክልሉ አስተማማኝ ሰላምና ደህንነት  እንዲረጋገጥ በልዩ ሁኔታ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ይደረጋል። አሁን የገጠመውን ፈተና ለመወጣት የድርጅቱ  አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም የክልሉና  የአገሪቱ ህዝቦች፣ ከመቼውም ጊዜ በላይ በአንድነት በመቆም የገጠመውን ፈተና በብቃት እንዲወጡ ጥሪ አቀርቧል። የተፈፀመው ጥቃትና ወንጀል ለመሸፋፈንና ለማሳነስ ሆን ተብሎ አሉባልታ በመንዛት ህዝቡን ለማደናገርና አቅጣጫ ለማሳት የሚሰሩ አካላት ከዚህ ዕኩይ ድርጊታችሁ እንዲቆጠቡ አዴፓ አሳስቧል። በመጨረሻ ለሰማዕታት ቤተሰቦች፣ ወዳጆች፣ ለመላው የአማራ ህዝብና የአገራችን ህዝቦች መፅናናትን  እንመኛለን፡፡ በአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ማዕከላዊ ኮሚቴ የተሰጠው መግለጫ ሙሉ ቃል                            እንደሚከተለው ቀርቧል የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ፅጌ አቀነባባሪነት ተሞክሮ ሙሉ በሙሉ በከሸፈው የመፈንቅለ መንግስት ሴራ፤ ሴራው ባስከተለው የክልሉ መሪዎች መስዋዕትነት እና በአገሪቱ የመከላከያ መኮንኖች ጥቃት እና መስዋዕትነት እንዲሁም ተያያዥ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ሰኔ 21 ቀን 2011 ዓ.ም አስቸኳይ ስብሰባ አካሂዷል፡ ማዕከላዊ ኮሚቴው ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባም በመፈንቅለ-መንግስቱ ሴራ ምክንያት መስዋዕትነት ለከፈሉ አመራሮች ቤተሰቦች፤ ወዳጆች፤ ለድርጅታችን አመራሮች፤ አባላትና ደጋፊዎች፤ ለክልላችንና የአገራችን ህዝቦች መፅናናትን ተመኝቷል፡፡ ማዕከላዊ ኮሚቴው ይህንን ዕኩይ ሴራ ለማክሸፍና የህግ የበላይነት መረጋገጥ ክቡር መስዋዕትነት ለከፈሉ  የክልላችን የፀጥታ አካላት እንዲሁም ክልሉን በማረጋጋት እገዛ እያደረጉ ላሉ የመከላከያ ሰራዊታችንና የፌደራል ፖሊስ አባላትና አመራሮች ምስጋና አቅርቧል፡፡ ማዕከላዊ ኮሚቴው ባደረገው ስብሰባ መፈንቅለ-መንግስቱን ያቀነባበሩና በድርጊቱ የተሳተፉ አካላት የፈፀሙት ድርጊት በክልሉ ዋና ዋና ተቋማት ማለትም የርዕሠ-መስተዳድር ጽህፈት ቤት፤ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን፤ የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅትን፤ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ጽህፈት ቤትን፤ የክልሉን ከፍተኛ አመራሮችና መኖሪያ ቦታዎች ለይቶ በማጥቃት የክልሉን መንግስት ለማስወገድ እና የክልሉን ህዝብ ለጥቃት ለማጋለጥ ያለመ መሆኑን ገምግሟል፡፡ ይህ ድርጊት ምንም አይነት የሞራል፤ የህግና የፖለቲካ አመክንዮ የሌለው ከመሆኑም በላይ አመራሮቻችን የተሰውበት ሁኔታ ግፍና ጭካኔ በተሞላበት መልኩ መሆኑ የአማራን ህዝብ ክብር የነካ እና ያዋረደ መሆኑ  በፅኑ የሚወገዝ ነው፡፡ ማዕከላዊ ኮሚቴው በስብሰባው ድርጅታችን የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በለውጡ ከታገለባቸው የህዝባችን ጥያቄዎች መካከል የዜጎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት እንዲከበር እንዲሁም ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ፅጌን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች በእስር ላይ እያሉ የመብት ጥሰት ይደርስባቸው የነበሩ ወገኖች ነፃ እንዲወጡ በግምባር ቀደምትነት የታገሉትን አመራሮች በግፍ እና በጭካኔ መግደል የእናት ጡት ነካሽነት እና ክህደት መሆኑን፤ ድርጊቱ የክልሉን መንግስትና ህዝብ እንዲሁም አገራችን ለከፋ አደጋ የሚያጋልጥ፤ የተጠናና በዕቅድ የተመራ፤ የራሱ አደረጃጀት የነበረው እና አገራዊ ስርዓቱን በሃይል በመናድ የመንግስት ስልጣንን በሃይል ለመቆጣጠር ተሞክሮ ሙሉ በሙሉ የከሸፈ መፈንቅለ-መንግስት መሆኑን፤ የመፈንቅለ-መንግስት ሙከራውን የፀጥታ ሃይላችን እና ህዝቡ ተረባርቦ ያከሸፈው ከመሆኑም በላይ የድርጊቱን ተሳታፊዎች አሳዶ እና በቁጥጥር ስር አውሎ የህግ የበላይነትን ያረጋገጠ መሆኑን፤ ይህ ድርጊት ከመፈጸሙ በፊት በክልላችን የተለያዩ አካባቢዎች ያጋጥሙ የነበሩ የህግ ጥሰቶች እና የሰላም እጦት እንዲታረሙና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ከህዝባችን ጋር ተግባብተን ወደ ተግባር በገባንበት ወቅት ይህ ድርጊት መፈፀሙ ድርጊቱ በአማራ ህዝብ ስም የተነገደ እና ህዝቡን ለጥቃት ያጋለጠ መሆኑን፤ ድርጅታችን የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ፅጌን ከእስር ከተፈታ በኋላ የድርጅታችን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሆኖ እንዲታገል፤ እንዲሁም የክልሉን ህዝብና መንግስት ሰላም እና ደህንነት እንዲያስጠብቅ የክልሉ መንግስት የሠላምና ደህንነት ቢሮ ኃላፊ ሆኖ እንዲያገለግል ኃላፊነት ተሰጥቶት ባለበት ይህን ድርጊት መፈፀሙ ከሞራል፤ ከህግ እና ፖለቲካዊ አቋም ተቃራኒ የሆነ ከባድ ክህደት መሆኑን፤ ድርጊቱም የአማራ ህዝብ ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲ እና መንግስት እንዳይኖረው እና በአገራችን የተጀመረው ለውጥ እንዲቀለበስ እና አገር እንዲፈርስ የማድረግ የጥፋት ሴራ መሆኑን ገምግሞ የሚከተለውን ባለ 6 ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥቷል፡፡ 1.በከሸፈው መፈንቅለ-መንግስት እጃቸው ያለበትን ግለሰቦችና ቡድኖች በህግ ቁጥጥር ስር የማዋል ስራችን በጸጥታ መዋቅሩና በህዝቡ ርብርብ፤ በአጠረ ጊዜና በተሳካ ሁኔታ የተፈፀመ መሆኑን የፀጥታ መዋቅራችንን ብቃትና ህዝባዊ መገንተኝነት ያሳየ፤ የህዝባችንን ሰላም ወዳድነትና ቀናዒነት ዳግም ያረጋገጠ አኩሪ ገድል ሲሆን አሁንም ወንጀለኞችን ሙሉ በሙሉ በህግ ቁጥጥር ስር የማዋል እና ህጋዊ እርምጃ የመውሰድ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ 2.ህዝባችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በህግ የበላይነት እጦት እና የሠላም መደፍረስ ምክንያት ለተለያዩ እንግልቶች እና ስጋቶች የተዳረገ መሆኑን በመገንዘብ የህግ የበላይነትን የማስከበር እንቅስቃሴ መጀመሩ ይታወሳል፡፡ በመሆኑም የፀጥታ መዋቅሩን መልሶ ለማጠናከር መላ ህባችንን በማስተባበር በክልሉ አስተማማኝ ሰላም እና ደህንነት እንዲረጋገጥ በልዩ ሁኔታ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ አስፈላጊው ሁሉ ህጋዊ እርምጃ ይወሰዳል፡፡ 3.አሁን የምንገኝበት ወቅት ለድርጅታችን፤ ለመንግስታችንና ለህዝባችን ፈታኝ እና ጠንካራ ውስጣዊ አንድነትን የሚጠይቅ ወቅት ነው፡፡ በመሆኑም መላ የድርጅታችን አመራሮች፤ አባላትና ደጋፊዎች፤ የክልላችንና የአገራችን ህዝቦች፤ ከመቼውም ጊዜ በላይ በአንድነት ቆመን የገጠመንን ፈተና በብቃት ለማለፍ እና አገራችንን ለመታደግ በፅናት እንድትቆሙ ጥሪያችንን እናቀርብላችኋለን፡፡ 4.በአሁኑ ወቅት ድርጅታችን፤ መንግስትና ህዝባችን ካጣናቸው ግምባር ቀደም መሪዎችና ከተፈፀመው ድርጊት ጋር ተያይዞ የተለያዩ የህዝባችንና የአገራችንን አንድነት አደጋ ላይ የሚጥሉ እና የተቀነባበሩ አሉቧልታዎች በመናፈሳቸው ህዝባችንን ሲያደናግሩ ይስተዋላል፡፡ በመሆኑም ህዝባችን ሆን ተብለው በሚነዙና ውስጣዊ ጥንካሬያችንን በሚጎዱ አሉቧልታዎች ሳይደናገር እና ሳይፈታ አንድነቱን ጠብቆ በፅናት እንዲቆም ጥሪ እናስተላልፋለን፡፡ 5.የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የተለያዩ አካላት በእንዲህ አይነት አገርና ህዝብ ችግር ላይ በወደቁበት ሁኔታ መረጋጋትን፤ ሠላምና አንድነትን የሚያጠናክሩ ስራዎች ላይ ማተኮርና በኃላፊነት ስሜት መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ምንም እንኳን ኃላፊነት የሚሰማቸውና ለሰላም የሚሰሩ የመኖራቸውን ያክል አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ እና ሌሎች አካላት በስመ የሃሳብ ነፃነት ህዝብን የሚያደናግሩ አሉቧልታዎችን ከመንዛት ባሻገር አጋጣሚውን ተጠቅመው ድብቅ አጀንዳዎችን ለማሳካት ሌት ከቀን በመስራት ላይ ናቸው፡፡ በመሆኑም በዚህ ድርጊት ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች አካላት ከአፍራሽ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ እያሳሰብን፤ ይህ ካልሆነ ግን ለህዝብና ለአገር ደህንነት ሲባል ማንኛውም አይነት ህጋዊ እርምጃ የሚወሰድ ይሆናል፡፡ 6.ሙሉ በሙሉ በከሸፈው መፈንቅለ መንግስት የተፈፀመው ጥቃት እና ወንጀል አንዲሁም የአመራሮቻችን የግፍ አገዳደል የአማራን ህዝብ ያሳፈረ እና ያዋረደ ሆኖ ሳለ ወንጀሉን ለመሸፋፈን እና ለማሳነስ ሆን ተብሎ አሉቧልታ በመንዛት ህዝባችንን ለማደናገር እና አቅጣጫ ለማሳት የምትሰሩ አካላት ከዚህ ዕኩይ ድርጊታችሁ እንድትቆጠቡ በጥብቅ እናሳስባለን፡፡ በመሆኑም መላው የክልላችን እና አገራችን ህዝቦች ወንጀል በአሉቧልታ ጋጋታ በፍፁም የማይሸፈን መሆኑን ተገንዝባችሁ በዚህ አይነት የወረደ ተግባር የተሰማሩ አካላትን በፅኑ እንድታወግዙ እና ትግል እንድታደርጉ ጥሪያችንን እያቀረብን ድርጅታችን የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲም የማስተካከያ እርምጃዎችን እየተከታተለ የሚወስድ መሆኑን እናሳስባለን፡፡ በመጨረሻም ተሞክሮ ሙሉ በሙሉ በከሸፈው መፈንቅለ መንግስት የኢትዮጵያን ህዝቦችና አገራዊ አንድነት አደጋ ላይ ለመጣል ታስቦ ተፈፀመ በመሆኑ ጥቃቱ በአማራ ክልል እና ህዝብ ላይ ብቻ የተቃጣ ሳይሆን በመላው ኢትዮጵያዊያን ላይ የተፈፀመ ጥፋት እና ሴራ ነው፡፡ በመሆኑም መላው የአገራችን ህዝቦች፤ የፓርቲያችን እህትና አጋር ድርጅቶች፤ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስታት፤ የኤርትራና የሱዳን ጎረቤት አገራት ተወካዮች፤ በገጠመን ችግር ከጎናችን በመቆማችሁ እና የተጎጂ ቤተሰቦችን በማፅናናታችሁ ድርጅታችን የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አክብሮቱንና ምስጋናውን ይገልፅላችኋል፡፡ እንዲሁም የፀጥታ መዋቅራችና መላ ህዝባችን በክልላችን ሁሉም አካባቢዎች ክልሉን ለማረጋጋት የተሰማራችሁ አመራሮች የመፈንቅለ-መንግስቱን ሙከራ ለማክሸፍ የህይወትና የአካል መስዋዕትነት የከፈላችሁ ሁሉ የፈፀማችሁት ገድል በደማቅ ታሪክ ተፅፎ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገር ሲሆን ድርጅታችን የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ህዝባችንን ከጎኑ በማሰለፍ የጀመረውን ህግና ስርዓት የማረጋገጥ እና ዋስትና ባለው ሰላም ውስጥ የህዝባችንን ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ትግሉን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ለማረጋገጥ እንወዳለን፡፡ በድጋሜ ለሰማዕታት ቤተሰቦች፤ ወዳጆች፤ ለመላው የአማራ ህዝብና የአገራችን ህዝቦች መፅናናትን እንመኛለን፡፡ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ሰኔ 22 ቀን 2011 ዓ.ም ባህር ዳር፤
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም