በክልሉ 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ወጣቶችን በክረምት የበጎ ፈቃድ ሥራ ለማሰማራት ዝግጅት ተጠናቋል

64
ሰኔ 22/2011 በአማራ ክልል 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ወጣቶችን በማሰማራት የክረምት በጎ ፍቃድ ሥራ ለማከናወን የቅድመ ዘግጅት ሥራዎች ማጠናቀቁን የክልሉ ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ። የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አባይነው መላኩ ለኢዜአ እንደገለጹት በተያዘው የክረምት ወቅት በበጎ ፈቃድ ተግባራት ከሚሳተፉት መካከል 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን የሚሆኑት በአማራ ዴሞክራሲአዊ ፓርቲ (አዴፓ) ወጣቶች ሊግ እና በአማራ ወጣቶች ማህበር አደረጃጀቶች የታቀፉ ናቸው። ከእነዚህ ተጨማሪም ከዩኒቨርሲቲ ተመላሽ ተማሪዎች፣ የከተማ ወጣቶችና አርሶ አደር ወጣቶች የሚሳተፉ ሲሆን የዩኒቨርሲቲ ወጣቶች ሌሎች ወጣቶችን የማስተባበር ሥራ እንደሚያከናውኑ አመልክተዋል። ከተሰሩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መካከል የበጎ ፈቃድ ስራዎችን ከሚያስፈጽሙ ተቋማት ጋር ስራዎችን ማቀድና ዕቅዱን መገምገም፣  ወጣቶቹ ከክልል እስከ ቀበሌ የሚሳተፉባቸውን ስራዎች መለየት እንዲሁም ወጣቶቹ በህጋዊ መንግድ ለመሳተፍ የሚያስችላቸውን የምዝገባ ቅጽ ማዘጋጀትና ሌሎችም ይገኙበታል። "በጎ ፍቃደኛ ወጣቶችም በተራቆቱ ቦታዎች ችግኝ መትከል፣ የአቅመ ደካሞች ቤት መጠገን፣ ለወባና ኮሌራ በሽታዎች መንስኤ ሊሆኑ ከሚችሉ ነገሮች ህብረተሰቡ እንዲጠነቀቅ ማስተማርና የጽዳት ስራዎችን ያከናውናሉ" ብለዋል። በተጨማሪም የትምህርት ቤት ወጪያቸውን በራሳቸው አቅም መሸፈን የማይችሉ ተማሪዎችን ለመርዳት የተለያዩ የትምህርት ቁሳቁሶችን የመደገፍና የተፈጥሮ ሃብት ስራዎችን የማጠናከር ስራዎች ይከናወናሉ። "በተለይ እንደ ክልል ወጣቱ የህግ የበላይነት እንዲከበር በማድረግ በኩል የማስተማርና አርያ የመሆን ምሳሌውን በአግባቡ እንዲወጣ የማድረጉ ጉዳይ በትኩረት ይከናወናል" ብለዋል። የበጎ ፍቃድ ንቅናቄው በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚጀመር ያስታወቁት ምክትል ቢሮ ኃላፊው ከሐምሌ 1 ቀን 2011 ዓ.ም እስከ ጳጉሜን 5 ቀን 2011 ዓ.ም ለተከታታይ ሁለት ወራት የበጎ ፈቃድ ሥራዎቹ እንደሚከናወኑ አብራርተዋል። በእነዚህ የልማት ሥራዎች በመንግስት ሊወጣ ይችላል ተብሎ የሚገመት 8 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ማዳን እንደሚቻልም አቶ አባይነው ጠቅሰዋል። በክልሉ በ2010 የክረምት ወቅት ከ4 ነጥብ 1 ሚሉዮን በላይ ወጣቶችን ለማሳተፍ ታቅዶ 80 ከመቶ የሚሆኑትን በተለያዩ ልማት ሥራዎች ማሳተፍ እንደተቻለ ታውቋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም