በኢትዮጵያ ክፍት የተደረገውን የቴሌኮም አገልግሎት ለመጠቀም የውጭ ኩባንያዎች እያኮበኮቡ ነው

138
ሰለሞን ተዘራ (ኢዜአ) በ1887 ዓም የዕድገትና የሥልጣኔ ፋና ወጊ የሆኑት ዳግማዊ ሚኒሊክ በሀገራችን የመጀመሪያ የሆነውንና ከአዲስ አበባ፡ሐረር ተዘርግቶ ለስልክ አገልግሎት ሥራ ላይ የዋለውን በመዳብ ሽቦ የሚሠራ የዘመኑን እንግዳ ነገር ሥራ ላይ ባዋሉበት ወቅት ከመሳፍንቱ፤ ከሹማምንቱና፤ ከመነኮሳቱ ክርክርና ተቃውሞ ገጥሞአቸው ነበር። ለዘመናት በመንግስት ይዞታነት የዘለቀው የኢትዮጵያ ቴሌኮሚኒኬሽን አገልግሎት ከመደበኛ ስልክ አገልግሎት በመነሳት በዘመን ሂደት አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ደርሷል። መንግስታት አገልግሎቱ ይሰጥ የነበረው በመንግስት ቁጥጥር በውጭ አገር ዜጎች አጋርነት ቢሆንም ቀስ በቀስ ዘርፉን በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች በመተካት መሻሻሎች ተደርገዋል። አሁን ላይ አለም የደረሰበትን ቴክኖለጂ ወደአገር ውስጥ ለማስገባት የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው። ለዚህ ይረዳ ዘንድ ኢትዮጵያ ቁልፍ የተባሉ የኢኮኖሚ ዘርፎችን ለውጭና የአገር ውስጥ ባለኃብቶች ክፍት ማድረጓን ተከትሎ አለም አቀፍ ስም ያላቸው ኩባንያዎች አይናቸውን አገሪቱ ላይ መጣል ጀምረዋል። በአዲስ የለውጥ ምዕራፍ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ መንግስት የቴሌኮሚኒኬሽኑን ዘርፍ ወደ ግል ለማዛወር ዕቅድ እንዳለው ገልጿል፡፡ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለፃ ይህ የማዛወር ሂደት የመንግስትንና የህዝብን ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ እንደሚካሄድ፣ በተለይም መንግስት ከፍተኛውን ድርሻ (Golden Share) በመውሰድ የግል ባለሀብቶች የሚያደርሱትን ተፅዕኖ እንደሚቋቋምና በዘርፉ ልምድ ያካበቱ የግል ኩባንያዎች ብቻ እንደሚሳተፉ ነው። ለዚህም ሃያ አንድ አባላትን የሚያካትት የመንግስት ኃብትን ወደግል ለማዛወር የሚያደርገውን ጥረት የሚከታተል ካውንስል ባለፈው ነሃሴ ወር ተቋቁሟል፡፡ በተጨማሪም መንግስት የቴሌኮም ህግን በማርቀቅና አዲስ የቴሌኮም ተቆጣጣሪ ድርጅት በማቋቋም ላይ ነው፡፡ ቴሌኮሚኒኬሽንን ወደግል የማዛወር እንቅስቃሴ በጣም ከፍተኛ ትኩረት ከሳቡት የመንግስት የቅርብ ለውጦች አንዱ ነው ፡ ፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መንግሰት ኢኮኖሚውን ከመንግስት ተጽእኖ ለማላቀቅ የወሰደው ትልቅ እርምጃ መሆኑን የኢኮኖሚ ተንታኞች ተስማምተውበታል። ኢትዮ-ቴሌኮም ለአገር ውስጥ እና  ለዓለም አቀፍ ባለሃብቶች ክፍት መደረጉ በአለም አቀፍ ደረጃ የበለጠ ተወዳዳሪ እንደሚያደርገው ታምኖበታል። የኢትዮጵያ መንግሰት የኢኮኖሚ ማሻሻያው የአገሪቱን ፈጣን እድገት ለማስቀጠል የሚያግዝ በመሆኑ ተግባራዊ መደረጉን ገልጿል። በዚህም በመንግስት ስር የሚተዳደሩትን  የባቡር አገልግሎት፣ ሆቴሎች፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ፣ እና የተለያዩ የማምረቻ  ተቋማትን ድርሻ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ለግል ባለሃብቶች የማስተላለፍ እቅድ አስቀምጧል። መንግስት በኢትዮ ቴሌኮም ፣የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣የባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክ  አገልግሎት ከፍተኛውን ድርሻ በመያዝ ቀሪውን ድርሻ የአገር ውስጥና የውጭ የግል ባለሃብቶች እንዲሳተፉበት እንደሚደረግም መግለጹ ይታወሳል። በኢትዮጵያ እየተከናወኑ የሚገኙ ሰፋፊ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን  ተከትሎ አገሪቱ ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ አገራት ላለፉት አስርት አመታት በተከታታይ ከ10 በመቶ የዘለለ እድገት እያስመዘገበች መሆኗን የአለም ባንክ በተደጋጋሚ የሚያወጣቸው ሪፖርቶች ያሳያሉ። አገሪቱ በነዚህ ስኬቶች ታጅባ ጉዞዋን ብትቀጥልም በመንግስት የበላይነት የሚከናወነው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እስከ ወዲያኛው በሚፈለገው ልክ እንደማይዘልቅ በመታመኑ ኢኮኖሚውን በከፊል ለግሉ ዘርፍ ክፍት ማድረግ አስፈልጓል። የብዙዎችን ቀልብ የሳበው ለምን ይሆን? ኢትዮጵያ ቴሌኮሚኒኬሽን በመንግስት ሞኖፖሊ ከተያዘባቸው ከአምስት የማይበልጡ አገሮች አንዷ ናት፡፡ የቴሌኮሚኒኬሽን አገልግሎት በግል ከሚሰጥባቸው ብዙ አገሮች እንደ ጎረቤቶቻችን ኬንያ፣ ሶማሊያና ሱዳን ያለው ዕድገት የሚያሳየው ይህ ዘርፍ ከመንግስት ይልቅ በግል፣ ከሞኖፖሊ ይልቅ በውድድር ላይ ቢመሰረት በጥራቱና በተደራሽነቱ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚቻል ነው። ይህን ተከትሎ ክፍት ከተደረጉት ዘርፎች አንዱ የሆነው የኢትዮ ቴሌኮም ልምድ ያካባቱ አለም አቀፍ ኩባንያዎችን ትኩረት ስቧል። ከጀርመኑ የቲ-ሞባይል (T-Mobile) ግሩፕ ጀምሮ እስከ ደቡብ አፍሪካው ኤም. ቲ. ኤን. (MTN) እንዲሁም የተለያዩ የአውሮፓና የኤስያ የቴሌኮም ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ካምፓኒዎች በኢትዮጵያ የቴሌኮሚኒኬሽን ገበያ ላይ ለመሳተፍ ከፍተኛ ፍላጎት አሳይቷል፡፡ ኢትዮጵያ ከአንድ መቶ አምስት ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ያላትና ኢኮኖሚዋ በፍጥነት እያደገ ካሉ አገሮች አንዷ ናት፡፡ በቴሌኮሚኒኬሽንና በፋይናንሱ ዘርፍ ምንም ትስስር የማይታይባት አገር እንደመሆኗ መጠን የተቀላጠፈ የቴሌኮም እድገት ድህነትን ለመቀነስና የሥራ ዕድል በመፍጠሩ ረገድ የሚያደርገው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው፡፡ የቴሌኮሚኒኬሽን ዘርፍ እድገት በእጅጉ ያንቀላፋውን የኢትዮጵያ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ከማነቃቃቱም በላይ እንደ አካውንቲንግ፣ ኢኮኖሚክስ፣ ማኔጅመንት የመሳሰሉትን ዘርፎች ስለሚያበረታታ በመቶዎች ለሚቆጠሩ የዩኒቨርስቲ ምሩቃን የሥራ እድል ለማመቻቸት ብሩህ ተስፋ እንደሰነቀ (“Risks and Opportunities of Late Telecom Privatization: The Case of Ethio Telecom” በሚል በዶ/ር ሊሻን አዳም የተጻፈው ጥናት ያሳያል። በአፍሪካ ከናይጀሪያ ቀጥላ በህዝብ ብዛት ሁለተኛ የሆነችው ኢትዮጵያ ለ100 ሚሊዮን ህዝቦቿ የምታቀርበው የተንቀሳቃሽና መደበኛ ስልክ አገልግሎት ለኩባንያዎቹ ሰፊ የገበያ እድል የሚፈጥር ነው። በአፍሪካ መሰረታቸውን ያደላደሉት ቮዳኮምና ኤም.ቲ.ኤን በአገሪቱ ያለውን እምቅ እድገትና አዳጊ ገበያ በመመልከት ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን በተለየ ሁኔታ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ። “ኢትዮጵያ ለእድገት ያላትን እምቅ አማራጭና አቅም ኤም.ቲ.ኤን በትኩረት ሲከታተል ነበር።የቴሌኮም አገልግሎቱ ለግሉ ዘርፍ ክፍት መደረጉ ለህዝቡና ለንግዱ ማህበረሰብ ከፍ ያለ ጠቀሜታ የሚያስገኝ ነው” በማለት የኤም.ቲ.ኤን ዋና ስራ አስፈጻሚ ሮብ ሸተር ለንደን ለሚገኘው የብሉምበርግ ዘጋቢ ተናግረዋል። “የኢትዮጵያ እምቅ ገበያ ክፍት በመሆኑ ኤም.ቲ.ኤን በጣም ተደንቋል ፤እድሉ ኩባንያው በፓን አፍሪካ ገበያ አሻራውን ለማስቀመጥ ትልቅ እድል የሚፈጥርለትም ነው ። እንቅስቃሴው በመንግስት ቁጥጥር ስር የሚገኙትን ኢትዮ ቴሌኮም፣ አቪየሽን፣ የባህር ትራንስፖርት አገልግሎትንና የሃይል አቅርቦቱን ለአገር ውስጥና ለውጭ ባለሃብቶች ክፍት ማድረጉን ተከትሎ  የታየ ፍላጎት ነው። " “ኢትዮጵያ ሳቢ የሆነ ገበያ እንዳላት ቮዳፎን በተደጋጋሚ ሲናገር ቆይቷል፤ይህን ተከትሎ ወደ አገሪቱ ለመግባት ፍላጎት እንዳለን አሳይተናል። እናም በኩባንያችን የኢንቨስትመንት መለኪያ በመታገዝ  ተሳታፊ ለመሆን እንሰራለን“ በማለት የኩባንያው ተጠሪ ለአይ.ቲ ድረ-ገጽ ተናግሯል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ስልጣን ከያዙ ከሁለት ወር በኋላ የተጀመረው የኢኮኖሚ ማሻሻያ በአገሪቱ ያለውን የስራ አጥ ቁጥር ለመቀነስ አላማ ያደረገ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል። ኤም.ቲ.ኤን እኤአ ከ2013 አንስቶ በኢትዮጵያ ወኪል ቢሮውን በመክፈት እድሉን ሲጠባበቅ መቆየቱን ዘገባው አመላክቷል። በቅርቡም ፈቃዱን በማደስ በዘርፉ በስፋት ለመሳተፍ እየተጠባበቀ ይገኛል። ኤም.ቲ.ኤን በ22 የአፍሪካና የእስያ አገሮች አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ሲሆን ቮዳፎን በአንጻሩ በ5 የአፍሪካ አገሮች አገልግሎቱን ይሰጣል። በአፍሪካ የአይ.ዲ.ሲ የቴሌኮምና ኢንተርኔት ዳይሬክተር የሆኑት ጆርጅ ካሌባላ ኢትዮጵያ በብዙ የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ኩባንያዎች ራዳር ውስጥ እንደነበረችና ከነዚህ መካከል ኤም.ቲ.ኤን እና ቮዳፎን በተለየ ሁኔታ አጋጣሚውን ሲጠባበቁ እንደነበር ተናግረዋል። “በአፍሪካ ትልቁና የመጨረሻው የቴሌኮም እድል እስከ አሁን በመንግስት ጠቅላይነት ተይዞ ቆይቷል” ብለዋል። “ኢትዮጰያ በአፍሪካ በህዝብ ብዛትና በፈጣን የኢኮኖሚ እድገት በመታጀቧ ዘርፉ ሰፊ እድል ያለበት ነው። ኢኮኖሚውን ተከትሎ ለመሰረተ ልማት ግንባታ ከፍተኛ በጀት ተመድቧል ፤ቴሌኮሙ ለግል ዘርፍ ክፍት መደረጉ ደግሞ ለኢኮኖሚ እድገቱ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ይኖረዋል” በማለት ጆርጅ ካሌባላ ተናግረዋል። የመንግስት ስትራቴጂ ተወዳዳሪነትን ሊገድብ ይችል ይሆን? የኢትዮጵያ መንግስት ለውጭ የሞባይል ስልክ አገልግሎት ሰጪዎች ፈቃድ ይስጥ አይስጥ ግልጽ ባይሆንም አሁን ባለው እውነታ የኢትዮ-ቴሌኮምን አነስተኛ ድርሻ ለመሸጥ መወሰኑ ግን እሙን ሆኗል። የአፍሪካ አናሊስት ዳይሬክተር ዶቤክ ፓተር እንደተናገሩት እድሉ ምንአልባት የውጭ አገልግሎት ሰጪ ኩባንያዎች በሙሉ አቅማቸው ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ ይገድባቸዋል። “መንግስት አብላጫውን ድርሻ መያዙ ዘርፉን በበላይነት ለመቆጣጠር እድል ስለሚሰጠው እንደ አንድ ችግር ሊታይ ይችላል። ብዙ የቴሌኮም ኩባንያዎች ትልቁን ድርሻ በመያዝ በኩባንያው ላይ የሚኖራቸውን ውሳኔ ሰጪነት ከፍ ማድረግ ይፈልጋሉ። ኤም.ቲ.ኤንና ቮዳኮም ኩባንያውን የማሳደግና የመምራት እድል የሚያገኙ ከሆነና ስትራቴጂውን ለመቅረጽ እድል ከተሰጣቸው ተሳታፊ ለመሆን ፍላጎት ሊያሳድሩ ይችላሉ” የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል። ጆርጅ ካሌባላ እንደሚስማሙት “ሁኔታው ሊሳካ የሚችለው መንግስት የቴሌኮም ገበያውን ነጻ ለማድረግ በሚወስደው እርምጃ ልክ ነው።” መንግስት በፕራይቬታይዜሽን እሳቤ ብዙውን ድርሻ ለመያዝ ወይም ገበያውን ክፍት በማድረግ አዲስ አገልግሎት የሚሰጡ አዳዲስ ኩባንያዎችን መጋበዝን መሻቱ ግልጽ አለመሆኑንም ባለሙያዎቹ ይናገራሉ። ኤም.ቲ.ኤንና ቮዳኮም ቀጣዩን አማራጭ እንደሚፈልጉ ጥርጥር የለውም የሚሉት ጆርጅ ካሌባላ የቴሌኮም ዘርፉን ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገርና የበለጠ ተወዳዳሪ ለማድረግ ይረዳቸዋል ባይ ናቸው። ስኬታማ የሆነ ተቋም እድሉን ካገኘ የአገሪቱን የሞባይል አገልግሎት በማሻሻልና የበለጠ ተደራሽ በማድረግ የዳታ አገልግሎት፣ 3ኛ ትውልድና 4 ኛ ትውልድ( 3 G and 4 G)የሞባይል አገልግሎት ለመስጠት ይችላል። “የመደበኛ የስልክ አገልግሎት መሰረተ ልማቶችን ለማሻሻልና ለማሳደግ የተመደበው ኢንቨስትመንት የብሮድባንድ የንግድ ትስስሩን  እንደሚያሳድገው ይታመናል።በተመሳሳይ ለብሮድባንድ መሰረተ ልማት  የሚመደበው  ኢንቨስትመንት በተለይ ፋይበርን መሰረት ያደረጉትን ተጨማሪ የዲጂታል አገልግሎትን ለምሳሌ ክላውድ፣ የዲጂታል ይዘት ያላቸውን አገልግሎቶች ያስፋፋል” በማለት ካሌባላ ተናግረዋል። ዶቤክ ፓተር እንደሚናገሩት ተቋማቱ በኢትዮጵያ የመስራት እድል ቢያገኙም እንኳን የረጅም ጊዜ ኢንቨስትመንት መመደብ ይጠበቅባቸዋል። የመጀመሪያው ጉዳይ በመንግስት ቁጥጥር ስር የነበረው የቴሌኮም አገልግሎት ክፍያ ለመንግስትና ለኢኮኖሚው ካለው ጠቀሜታ አንፃርና ውድድር ባለመኖሩ ከፍተኛ በመሆኑ እድገቱን አዝጋሚ ሊያደርገው ይችላል። በኢትዮጵያ የቴሌኮም አገልግሎት በአፍሪካ እግራቸውን ማስገባት የሚፈልጉ የሌሎች ግዙፍ ኩባንያዎቸን ትኩረት መሳቡን ካሌባላ ይናገራሉ። "ኦሬንጅ፣ ኤርቴል፣ ቻይና ቴሌኮም፣የአንጎላው ዩኒቴል እና ሞቪቴል ጉዳዩን በትኩረት እየተከታተሉት ይገኛሉ። ከዚህ በተጨማሪ የአገር ወስጥ ባለሃብቶች ከውጭ ኩባንያዎች ጋር በመጣመር ለመሳተፍ ፍላጎት አላቸው” በማለት ካሌባላ ገልጸዋል። “በቴሌኮም አገልግሎቱ ላይ የሚደረገው ማሻሻያና ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ያለጥርጥር የአገልግሎቱን ተጠቃሚዎች እና ኢንተርፕራይዞች የሚያስደስት” መሆኑንም  ጠቅሰዋል። ከዝቅተኛ ደረጃ የተነሳው የቴሌኮሚኒኬሽን ዘርፍ ባለፉት አስርት አመታት ጥሩ እድገት አሳይቷል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በ1994 እና በ2005 ከቻይና መንግስት የተበደረውን 3.1 ቢሊዮን ዶላር መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ የሞባይል ተጠቃሚዎችን ቁጥር በእጅጉ ከማሳደጉም በላይ ከ6000 ኪ.ሜ በላይ መሬት ውስጥ የተቀበረ ፋይበር በመዘርጋት አገሪቷን በዘመናዊ የኮሚኒኬሽን መስመር ለማዳረስ ጥረት አድርጓል፡፡ የኢትዮ ቴሌኮም ድህረ ገፅ እንደሚያሳው የሞባይል ሲም ካርድ የገዙ ደንበኞች ቁጥር 65.7 ሚሊዮን ደርሷል፡፡ ከነዚህ ውስጥ ወደ 40 ሚሊዮን የሚጠጉ እውነተኛ የሞባይል አገልግሎት ተጠቃሚዎች ናቸው ተብሎ ይገመታል፡፡ ወደ 18 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑት ሲም ካርዶች እንደገና ለገበያ የሚውሉ ናቸው፡፡በዚያኑ ልክ የሞባይል ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር አድጓል፡፤ ከሞባይል ተጠቃሚዎች ግማሾቹ (ወደ 20 ሚሊዮን የሚሆኑት) የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ናቸው ተብሎ ይገመታል፡፡ የሞባይልና የኢንተርኔት አገልግሎት 92 በመቶ የሚሆነውን የኢትዮ ቴሌኮም አመታዊ ገቢ የሚያስገኙ ከመሆናቸውም በላይ በፍጥነት በማደግ ላይ ያሉ አገልግሎቶች ናቸው ፡፡ በገቢ አንፃር ሲታይ ምንም እንኳን የኢትዮ ቴሌኮም አመታዊ ገቢ እያደገ ቢመጣም በአንፃራዊነት በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ለምሳሌ በ2010 የኢትዮ ቴሌኮም ገቢ 38 ቢሊዮን ብር (1.4 ቢሊዮን ዶላር) ሲሆን የሳፋሪ ቴሌኮም ገቢ 2.1 ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ይህም ማለት የኬኒያው ሳፋሪ ኮም በ29.5 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች ብቻ፤ከ65 ሚሊዮን ተጠቃሚ ያለውን የኢትዮጵያውን ቴሌኮም ካምፓኒ በአንድ ነጥብ አምስት እጥፍ በልጦታል ማለት ነው፡፡ በዚህ ንፅፅር የኢትዮ ቴሌኮም ገቢ በሶስት እጥፍ ማደግ ነበረበት፡፡ (“Risks and Opportunities of Late Telecom Privatization: The Case of Ethio Telecom” በሚል በዶ/ር ሊሻን አዳም ከተፃፈው የተወሰደ)    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም