የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በበጋ ወራትም ተጠናክሮ ይቀጥላል

59

ሰኔ 22/2011 የክረምት የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በበጋ ወራትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ገለጸ፡፡

የኮሚሽኑ የደን ዘርፍ ልማት ፕሮግራም አስተባባሪ ዶክተር ተፈራ መንግስቱ  እንዳሉት   በክረምት የተተከሉ ችግኞችን ከመንከባከብ ጎን ለጎን የአዳዲስ ችግኖች ተከላ በበጋው ወራትም ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

ለችግኝ  ልማት ተስማሚነት ባላቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች የአትክልት ና ፍራፍሬ ችግኞች የእንስሳት መኖ እጽዋት በበጋው ወራት ከሚተከሉ የችግኝ አይነትቶች መካከል እንደሚገኙበት  ጠቅሰዋል፡፡

በበጋው ወራት የሚተከሉ አትክልትና ፍራፍሬ ችግኞች ለአረንጓዴ ልማት አስተዋጽኦ ከማበርከታቸው ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸው የጎላ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

የእንስሳት መኖ ዕጽዋት የመሬት ለምነትን በመጠበቅ ላቅ ያለ አስተዋጽኦ አለው ያሉት አስተባባሪው የእንስሳት ቀለብን ከማሟላት አኳያም ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

በጋው የችግኝ ተከላ በከተሞች ጭምር እንደሚከናወን ጠቅሰው አረንጓዴ ቦታዎችን ለታለመላቸው አላማ ማዋል እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

የከተሞች መስፋት ብቻውን ለትውልዱ ተስፋ ሊሆን አይችልም ያሉት ዶክተር ተፈራ  ለአረንጓዴ ቦታዎች ትኩረት ሰጥቶ መሰራት እንዳለበትም ነው ያብራሩት፡፡

“የሌሎች ሀገራት ህዝቦች  ሀገር እየፈጠሩ ለትውልድ ያስተላልፋሉ፤ እኛ ደግሞ በአንጸሩ በተፈጥሮ የታደለችውን ሃገራችንን  በአግባቡ ባለመያዛችን እያጎሳቆልናት ነው” ብለዋል፡፡

የችግኝ የተከሉ አካሉ አካላት ተንከባክቦ ማሳዳግ እንዳለባቸው ገልጸው  ኮሚሽኑም በተለያዩ አካባቢዎች  ለተተከሉ ችግኞች ክትትል እንደሚያደርግም ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች በዘመቻ ቢተከሉም ከፖለቲካ ትርፍ ባለፈ ደኖችን ከመመናመን፣ አካባቢን ከመራቆት፣ ሃይቆችን ከመድረቅና በደለል ከመሞላት እንዳልታደጋቸውም ተናግረዋል።

ቀደም ሲል የነበሩ ችግሮችን በመፍታት ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት፣ የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻልና ምርታማነትን ለማሳደግ የተጠና የደን ልማት መርሃ ግብር አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የሀገሪቱን ዜጎች የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከተለመደው የክረምት ወቅት የዘመቻ ሥራ ወጥቶ በበጋ ወራትም ቀጣይነት ባለው መልኩ  መሰራት እንዳለበት ነው ዶክተር ተፈራ የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም