የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ከጃፓን የውጭ ንግድ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጋር ተወያዩ

55
ሰኔ 22/2011 የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አክሊሉ ኃይለሚካኤል እና የጃፓን የውጭ ንግድ ድርጅት (JETRO ) ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር ሂራኖ ካትሱሚን በሁለቱ አገራት መካከል ያለው የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት በሚጠናከርበት መንገድ ላይ ተወያዩ። ባለስልጣናቱ አዲስ አበባ ውስጥ ባደረጉት ውይይት የሁለቱን አገሮች የረጅም ጊዜ የትብብር ግንኙነት በንግድ እና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ማጠናከር በሚቻሉባቸው ጉዳዮች መክረዋል። የኢትዮጵያና የአፍሪካ የቢዝነስ አካላት በቀጣይ በጃፓን ቶክዩ ከተማ በሚካሄደው ዓለም አቀፍ ፎረም /TICAD/ ላይ መሳተፍ እንዲችሉ በመንግሥት በኩል ድጋፍ እንዲደረግ ዶክተር ሂራን ጥያቄ አቅርበዋል። ዶክተር አክሊሉ በበኩላቸው ጃፓን ከኢትዮጵያ ጋር መልካም ግንኙነት እንዳላት በማስታወስ፣ በቶክዮ በሚካሄደው ጉባኤ መሳተፍ በአፍሪካና በጃፓን የቢዝነስ አካላት መካከል የመረጃና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ከፍተኛ እገዛ ያለው በመሆኑ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል። ከጃፓን የውጭ ንግድ ድርጅት ጋር በመተባበር በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የኢንቨስትመንት፣ የንግድና የቱሪዝም እንቅስቃሴ ይበልጥ ማሳደግ እንደሚገባም ሚኒስትር ዴአታው ገልጸዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም