በስልጤ ዞን በተፈጥሮ አደጋዎች ጉዳት የደረሰባቸውን መልሶ ለማቋቋም እየተሰራ ነው

135
ሰኔ 22/2011 በስልጤ ዞን ከሚያዚያ ወር ጀምሮ በደረሱ የተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን የሕብረተሰብ ክፍሎች መልሶ የማቋቋም ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት መምሪያ አስታወቀ ፡፡ የመምሪያው ምክትልና የተፈጥሮ ዘርፍ ኃላፊ አቶ መሀመድ ፈርጌሳ እንደገለጹት በዞኑ ከሚያዚያ ወር ጀምሮ በስድስት ወረዳዎች ላይ የጎርፍ አደጋዎች ተከስተዋል፡፡ እነዚህ አደጋዎች የሰው ሕይወት ከማጥፋታቸው በተማሪ ከፍተኛ የሆነ የንብረት ውደመትና የቤት እንስሳት ሞትን ያስከተሉ ሲሆን በርካቶችን ለመፈናቀል ዳርገዋል ፡፡ አብዛኛው የዞኑ መልክአ ምድር በስምጥ ሸለቆ ተፋሰስ ውስጥ የሚገኝ መሆኑና የዞኑ የደን ሽፋን መመናመን እየደረሱ ላሉ የተፈጥሮ አደጋዎች ዋንኛ ምክንያት መሆናቸውንም አቶ መሀመድ ተናግረዋል ፡፡ እንደ አቶ መሀመድ ገለፃ በተከሰቱት በነዚህ አደጋዎች የስድስት ሰዎች ሕይወት ሲጠፋ 2 ሺህ 8 የቤት እንስሳት በጎርፍ ተወስደው ሞተዋል ፡፡ በአደጋው በርካታ ቤቶች በተለያየ ደረጃ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 73 ቤቶች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል ፡፡ “ ከ10 ሺህ በላይ ነዋሪዎችም ለመፈናቀል ተዳርጓል” ብለዋል ፡፡ ጉዳት የደረሰባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች መልሶ ለማቋቋም እየተደረገ ባለው ጥረት ከዞን እስከ ፌዴራል ያሉ የሚመለከታቸው አካላትና የተለያዩ ተቋማት በርካታ ሥራዎችን እያከናወኑ መሆናቸውን የገለጹት ምክትል የመምሪያው ኃላፊ ከነዚህ ሥራዎች ጎን ለጎን በማሽነሪና በሰው ጉልበት የቅድመ መከላከል ሥራ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ እንደ አቶ መሀመድ ገለጻ በአደጋዎቹ ለተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎች ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች የቀረበላቸው ሲሆን ሁሉም ተፈናቃዮች ከጊዜያዊ መጠለያ ወጥተው ወደየቀያቸው እንዲመለሱ ተደርጓል ፡፡ ሙሉ በሙሉ ከወደሙ 73 ቤቶች ውስጥ የ33 ቤቶች ግንባታ ተጠናቆ ወደቄያቸው የተመለሱት ተፈናቃዮች እንዲኖሩባቸው የተደረገ ሲሆን ቀሪ 40 ቤቶች ደግሞ በግንባታ ላይ ይገኛሉ ፡፡ ማሳቸው ለተጎዳባቸው አርሶ አደሮች እስካሁን ድረስ 600 ኩንታል ምርጥ ዘር መቀረቡንና ሌላ 96 ኩንታል ደግሞ ለስርጭት ተዘጋጅቷል ፡፡ "ከብቶች ለሞቱባቸውም ለአንድ ቤተሰብ ከ20 እስከ 30 ሺህ ብር የሚያወጡ የተሻሻሉ የከብት ዝርያዎችን ለማቅረብ እየተሰራ ነው" ብለዋል ፡፡ አቶ መሀመድ እንዳሉት እስካሁን ከተለየው 96 ኪሎ ሜትር ለጎርፍ ተጋላጭ የሆነ ሥፍራ በማሽን በመታገዝ ከ13 ኪሎ ሜትር በላይ የማስተካከያ ሥራ ተሰርቷል፡፡ በዞኑ በተፋሰስ  ልማት ሥራ 42 ሺህ 900 ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ የአፈርና ውሃ እቀባ ተግባራት መከናወናቸውን የተናገሩት አቶ መሀመድ በእዚህም 102 ሚሊዮን ለኢኮኖሚና ለሥነ-ምህዳር ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ተዘጋጅተው የተከላ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል ፡፡ በዞኑ ስልጤ ወረዳ የጠቀር ቀበሌ ነዋሪው አቶ ሱንካሞ ሹራላ በበኩላቸው ባለፈው ሚያዝያ 07 ቀን 2011 ምሽት ላይ በተከሰተ የጎርፍ አደጋ ንብረታቸውንና ከብቶቻቸውን አጥተዋል፡፡ ከእዚህ በፊት እንዲህ አይነት አደጋ ገጥማቸው እንደማያውቅ የሚናገሩት አቶ ሱንካሞ የእሳቸውና የባለቤታቸው ሕይወት በአጋጣሚ መትረፍ ቢችልም ጎርፉ በአቅራቢያቸው የሚኖሩ የሶስት የልጅ ልጆቻቸውን ሕይወት እንደነጠቃቸው አስታውሰዋል፡፡ ከአደጋው በኋላ መንግስትና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ሲያደርጉላቸው መቆየታቸውን ገልጸው፣ ምግብና መጠለያ በወቅቱ ማግኘታቸውን አብራርተዋል ፡፡ በወደመባቸው ምትክ እየተገነባላቸው ያለው መኖሪያ ቤትም በአሁኑ ወቅት ተሰርቶ እየተጠናቀቀ ሲያዩ መፅናናታቸውን ተናግረዋል ፡፡ ወጣት መሀመድ ሱንካሞ በበኩሉ የጎርፍ አደጋው ሲከሰት ከልጁና ከባለቤቱ ጋር እንደነበርና እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ሕይወታቸው ሊተርፍ መቻሉን አስረድቷል ፡፡ የጎርፍ አደጋው የተከሰተው በዋናነት በአካባቢው የነበረው ደን እየተመናመነ በመምጣቱ እንደሆነ መገንዘቡን የተናገረው ወጣቱ በአሁኑ ወቅት ከአካባቢው ወጣቶች ጋር በመተባበር የችግኝ ተከላ ሥራ ለማከናወን በዝግጅት ላይ መሆናቸውን አስረድቷል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም