ባለስልጣኑ የሸማቾችን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ ቅንጅታዊ አስራርን ለመዘርጋት እየተንቀሳቀስኩ ነው አለ

79
አዳማ ሰኔ 21ቀን 2011 የሸማቾችን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ ቅንጅታዊ አስራርን ለመዘርጋት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን አስታወቀ። ባለስልጣኑ በአገሪቱ የንግድ ሥርዓት ውስጥ ነፃና ፍትሐዊ የንግድ ውድድር ከማስፈንና የሸማቾችን መብትና ጥቅም ከማስጠበቅ አኳያ ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚሰራበትን የመነሻ ሰነድ ዛሬ ይፏ አድርጓል። የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ተወካይ ወይዘሮ መሰለች ወዳጆ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ባለስልጣኑ የሸማቹን መብትና ጥቅም ከማስጠበቅ አኳያና ነፃና ፍትሐዊ የንግድ ውድድር እንዲሰፍን ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ ለመሥራት ጥረት እያደረገ ነው። በዚህም ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር ከሕግ አወጣጥ በተገናኘ እየተከናወኑ ያሉትን ተግባራት ያከናውናል። ከፖሊስ ጋር በሚፈጠረው ቅንጅት ከሸማቾች መብት ጥበቃ ተያይዘው የሚነሱ የወንጀል ጉዳዮችን በመከታተል እንደሚሰራም ገልጸዋል። ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በጥናትና ምርምር  ሥራዎች ላይ ተቀናጅቶ ለመሥራት መዘጋጀቱን አስረድተዋል። ባለስልጣኑ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በጋራና በቅንጅት ሊሰራ ስለሚችልበት ሁኔታና አግባብ አቅጣጫ የሚያስቀምጥ ሰነድ ማዘጋጀቱን አመልክተው፣ አስፈፃሚ አካላቱ የተሰጣቸውን ተግባርና ኃላፊነት ተገንዝበው ለተፈጻሚነቱ እንዲረባረቡ ጠይቀዋል። የባለስልጣኑ የሕግ ባለሙያ አቶ ዮናስ አበበ በበኩላቸው በባለሥልጣኑ ሰነዱ በአገሪቱ የንግድ ስርዓት ውስጥ ነፃና ፍትሐዊ የንግድ ውድድር ከማስፈንና የሸማቾችን መብትና ጥቅም ከማስጠበቅ አኳያ ባለስልጣኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት  የሚሰራበትን አግባብ ያመላክታል  ብለዋል። በተለይ ሰነዱ ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ተቋማት የበኩላቸውን አስተዋፅዖ በማድረግ ሚናቸውን እንዲወጡና የተጣለባቸውን ኃላፊነት በቅንጅትና በጋራ እንዲወጡ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር አስታውቀዋል። በተለይ ከነዚህ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት በተቋማቱ የሚጋጩ ውሳኔዎች እንዳይወሰኑና የጥቅም ግጭቶች እንዳይኖሩ ከማድረግ ባለፈ በተቋማቱ መካከል የተግባራት ድግግሞሽ ለማስቀረት እንደሚያስችል  አብራርተዋል። ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሥነ ልክ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱ አባጊቤ ነፃና ፍትሐዊ የንግድ ውድድር የሰፈነበት ሀገር ለመገንባትና የሸማቾች መብትና ጥቅም የተከበረበት ገበያን የመፍጠርና የማሳደግ ጉዳይ ለአንድ ተቋም ብቻ የሚተው ኃላፊነት ባለመሆኑ ሁሉም አካላት ተቀራርበው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል። ሰነዱ በየደረጃው የቅንጅት አሰራር ለማስፈን፣ ሸማቾችን ተጠቃሚ የሚያደርግና የንግድ ውድድሩን የሚያሳልጥ በመሆኑ ለተፈጻሚነቱ ተቀራርበን እንሰራለን ነው ያሉት። ሌላው ተሳታፊ በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ የንግድ ውድድርና ሸማቾች ወንጀል ምርመራ ዳይሬክተር ፀጋይ ወልደሩፋኤል ሰነዱ በባለስልጣኑም ሆነ በሌሎች አካላት የሚታየውን ተደጋጋሚ ሥራዎች ሊያስቀር ይገባል ይላሉ። ይህን ማድረግ ከተቻለ በየዘርፉ የሚስተዋሉትን ጸረ- ውድድር ተግባራትና የሸማች መብት ጥሰቶች በመቀነስ ረገድ የማይተካ ሚና እንዳለው ተናግረዋል። ለአንድ ቀን በአዳማ ከተማ በተዘጋጀው በዚሁ መድረክ ላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትህ፣የንግድና ኢንዱስትሪ ቋሚ ኮሚቴ አባላትን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም