ዛሬ ላይ ነገን ስፈልጋት

104

ጌታቸው ሰናይ (ኢዜአ)

ኢትዮጵያችን ስንት ጊዜ ትዘን? ስንት ጊዜ ታልቅስ? ስንት ጊዜ በአቤልና ቃዬል ትንሰቅሰቅ? ስንት ጊዜ እናት መቀነቷን አስራ ስለልጆቿ ታንባ? ከአንዱ ወደ ሌላው በለውጥ ስንሸጋገር ህይወት እየከፈልን መምጣታችን በእጅጉ ያሳስባል።

የዛሬው ከትናንቱ ካልተለየ ምን ለውጥ አመጣን? አዲስ ትውልድ በሰከነ፣ በተረጋጋና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ የአባቶቹን የታሪክ ትርክት ሳይፈትሽ ያንኑ ከደገመ የ21ኛው ክፍለ ዘመንን እንዴት ሊመጥን ይችላል? በመዝገበ ቃላቱ “ጀግንነት” የሚለውን ቃል ትርጓሜ ካልቀየረ “እምዬ ኢትዮጵያ” ማለትስ እንዴት ያስችለዋል?  የ"ጀግንነት" ልኩና መገለጫው በመሰረተ ሃሳብ ደረጃ መቀየር ግድ ያለን ዘመን ላይ መሆናችንን ካልተገነዘብን 21ኛው ክፍለ ዘመን መግባታችን በምን ይታወቃል?

የኢትዮጵያን ፖለቲካ ሂደት የመጠላለፍ፣ አንዱ ሌላውን የማሳደድ፣ ገድሎ ማቅራራት የሚስተዋልበት መሆኑን ተረድቻለሁ። የአሸናፊነት የታሪካ ትርክታችን በደም ጅረት የተጻፈ ነው። ወንድም ወንድሙን በመግደል  “ለአገር አንድነትና ነጻነት ነው ያደረግኩት” በማለት እየፎከርን ዘመናትን አልፈናል፤ እያለፍን ነው። ዛሬም በተመሳሳይ መንገድ ይደረጋል። የእኛን ትርክት የደገፈልን ቢሞትም ጀግናችን ነው፤ ያልደገፈ ደግሞ ታሪካዊ ጠላታችን ይሆናል። በሌላ ጊዜ ታሪክ ሲገላበጥ ገዳይና ተገዳይ ሲቀያየሩ ትርክቱ ይቀየራል። ይህ ወደ ዘመን መቀመቅ ይዞን እየተጓዘ ያለ የታሪክ ትርክት በዘመናት ሊጠግ የማይችል የድህነት ቁስልን እንድንለብስ ያደረገንን መለስ ብለን ካላጤነው አደጋው የከፋ ነው።

አንዳንዴ ሳስበው የውጭ ጠላት አጥቅቶን ካደረሰብን ጉዳት ይልቅ አንዳችን በሌላችን ላይ ያደረስነው የከፋ ነው። “የስልጣኔ ማማ ላይ ደርሰን ነበር” ብለን የምንፎክረውን ያህል እርስ በርሳችን በመጠፋፋት የአገራችንን  መጻኢ እድል ያጨለምነው ይበዛል። አገሪቷ ያላትን ሀብት አፍስሳ ለነገ ብሩህ ተስፋ ይሆናሉ ያለቻቸውን እንቁዎች እየቀጠፍን የመጣንበት መንገድ ከየትኛውም የውጭ ጠላት ሴራ ቢበልጥ እንጂ አያንስም።

ለእኔ የታሪክ ትርክቶቻችን የመጠፋፋት መንስኤዎቻችን ናቸው። አንደኛው ስለራሱ ማንነትና ስሌላው  የሚተርከው የታሪክ ትርክት በዘመን ጅረት እየፈሰሰ መጥቶ አንዱ ሌላውን ለማጥፋት መንስኤ እየሆነ ዛሬ ላይ ደርሰናል። ከ1950ዎቹ ጀምረን ብናይ ኢትዮጵያ አሉኝ የምትላቸው ብሩህ ልጆቿን በገዛ ልጆቿ በመጠላለፍ ፖለቲካ አጥታለች። በታላቅና ታናሽ ወንድማማችነት ስሜት ቁጭብሎ ከመነጋገር ይልቅ ጦር ሰብቆ፣ ጎራዴ መዞ፣ መሳሪያ ተኩሶ ወንድሙን በመግደል “ጀግና” የሚል ስያሜን ማግኘት ለታሪክ ትርክታችን ማድመቂያ አድርገናል። ሀሳባቸው አልተመቸንም፣ አስተዳደራቸው አይመጥነንም በማለት የቀጠፍናቸው። ለሶስት ሺህ ዘመን ያልተላቀቀን ረሃብን፣ መሀይምነትን ከአገራችን አጥፍተን ወደ ቀድሞው የስልጣኔ ማማ ከመድረስ ይልቅ በታሪክ ትርክት ውስጥ አንዱ ከሌላው በላይ ጀግና ለመባል ወንድሙን የሚገልበት ሁኔታ ዛሬም እንዳለቀቀን እናስተውላለን።

ኢትዮጵያዊ ነን፤ ለጠላታችን በምንም ምክንያት የማንበገር ጀግኖች። ግን ጠላታችን ማነው? እውን ጠላታችን  የውጭ ወራሪ ነው? ቁጭ ብለን ልናስበው የሚገባ ነገር ነው። በአገራችን ከ1900 ጀምሮ ከውጪ በመጡ ወራሪ ሃይሎች ጋር በተካሄዱ ጦርነቶች ምክንያት ካጣናቸው ዜጎቻችን ይልቅ በእርስ በርስ ያጣናቸው አይበልጥምን? በእዚህ ጊዜ ውስጥ ግን እርስ በርስ ባደረግነው ግጭት፣ በመገዳደል ያለቀብን የሰው ሃይል በቁጥር ቢበልጥ እንጂ አይተናነስም። በዚህ ትርክት ውስጥ ከወራሪ ጠላት የሚከፋው በአስተሳሰብ ልዩነት ብቻ ወንድም ወንድሙን መግደሉ ቅስም ይሰብራል። የቁጥሩ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን አርአያን ነጥሎ መምታቱ ደግሞ አንጀት ይበጥሳል። ለምንድን ነው? እንደዚህ የሆነው ብለን ስንጠይቅ የምናገኘው ምላሽ ብዙዎችን ያስደንቃል።

መደማመጥ አንችልም። የመደማመጥ ክህሎት የለንም። አንዳችን የሌላችንን ታሪካዊ፣ ማንነታዊ ትርክት  ማዳመጥ አንችልም። በጥሞና ታሪኩን ስለማንሰማውም ማንነቱን ለመቀበል ያቅተናል። ሰው በማንነቱ ስንቀበለው እኛ ከምንተርከው ማንነት ያነስን ይመስለናል። እኛ የራሳችንን ማንንት ስንተርክ ከሌላው የተሻለ አድርጎ ለማሳየት የምንሞክረውም ለዚህ ነው። በሳይንሳዊ እይታ ሰው ከሰው የሚለይበት ምንም አይነት ነቁጥ ምክንያት ባይኖርም በዘመናት የገነባው ለራስ ያለ ታሪካዊና ማንነታዊ ትርክት ልዩ መሆናችንን ይነግረናል። ልዩ መሆናችንን ሌላው እንዲያምንልን ጫና ለመፍጠር እንሞክራለን። ከአስተሳሰብ ባሻገር በመሳሪያ ያንን ማንነት ሰዎች እንዲቀበሉት ለማድረግ ይሞክራል። መደማመጥ አንችልም፤ ያለመደማመጣችን መሳሪያ ያማዝዘናል።

ስለራሳችን የምናውቀው ጥቂት ነው። ስለማንንታችን የምንረዳውም በዚያው መጠን ውስን ነው። ነገር ግን ውስኑን ማንነታችንን አግዝፈን በማየት ለመጠፋፋት መንስኤ እንሆናለን። በመልከአምድራዊ አቀማመጥ፣ በቋንቋ፣  በስነልቦና የምንለያይባቸው ከባቢያዊ ሁኔታዎች አሉ ማለት አንዳችን በሌላችን ውስጥ አንታይም የሚል መደምደሚያ ላይ አያደርስም። ከአንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ዓመት በፊት ህይወቷ ያለፈውና የሰው ልጆች እናት አድርገን የምንወስዳት “ሉሲ” በእናትነት እያየን እርስ በርስ ግን የልዩነን ትርክት ማየት ያላዋቂነታችን ጫፍ የሚያረጋግጥ ነው። እርስ በርስ የተሳሰር በዲ.ኤን.ኤን የማንለያይ መሆናችን ሳይንስ ባረጋገጠልንና ባስተማመነን መጠን እኛ በታሪክ ትርክቶቻችን የተለየን መሆናችንን ለማረጋገጥ እንሞክራለን። ባለፉት ዘመናት የመበዳደል ታሪክ እንካሳለን።

ቅድም አያቶቻችን፣ አያቶቻችን ተበዳድለው ይሆናል፤ በዚያን ዘመን በነበረው አስተሳሰብ የመንግስት አመሰራረት አማካኝነት አንዳቸው ሌለኛቸው ላይ በደል ሰርተዋል ብለን እናምን ይሆናል፤ ዛሬ ላይ ግን ይህ ሊያወቃቅሰን፤ ሊያጋድለን አይገባም። አንድን ከዘመናት በፊት የተሰራን በደል እየቆጠሩ መሳሪያ መማዘዝ፣ አንዱ ሌላውን መኮነን፣ መግደልና “ከአጠገቤ ጥፋ እንዳላይህ” ማለት ለ21ኛውክፍለ ዘመን በማይመጥን አስተሳሰብ ውስጥ መሆናችንን ያመላክታል። መገዳደልና በአሸናፊነት ወደፊት መምጣት የጀግንነት አካል ተደርጎ እንዲወሰድ መተረክም ዘመኑን አለመዋጀት ነው። ወንድሙን በመግደል እርሱ የተሻለ መሆኑን ለማሳየት ይሞክራል።

ኢትዮጵያ በዘመኗ ውስጥ ያሳለፈችው ፈተና እጅግ ብዙ ነው። አዋቂዎቿን፣ ችግሮችን ያሻገሯትን በገዛ ልጆቿ አጥታለች። በ1953 ዓ.ም በታህሳስ ግርግር ንጉሱን ለማውረድ በማሰብ እርሳቸው ወደ ውጭ አገር በሄዱበት  ወቅት በተፈጸመው ድርጊት በርካታ ዜጎች አልቀዋል። የንጉሱ ዘመን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁኔታውን የሚመሩት ሹመኞች ለእዚያ ዘመን ህዝብ አለመመጠን ያስከፈለው ዋጋ አገሪቷ ላለመረጋጋትና አንዱ ሌላውን ላለማመን በርከፋች እንደነበር ከ15 ዓመታት በኋላ የተፈጸመው መፈንቅለ መንግስት ማሳያ ሊሆን ይችላል።

በ1966 ዓ.ም የተፈጸመው መፈንቅለ መንግስት በፖለቲካው፣ በማህበራዊና በኢኮኖሚው ዘርፍ ያመጣው መዘዝ በቀላሉ የሚገመት አይደለም። በርካታ ጥናቶችና ታሪካዊ ትንተናዎች ይፈልጋል። በቁንጽል ካየነው ግን የንጉሱ ሚኒስትሮች፣ መኳንት፣ ባለሀብት መገደል በቀላሉ የሚታይ ችግር አልነበረም። አገር ዋጋ ከፍላ በውስጥና በውጪ ያስተማረቻቸው ልጆቿ ሲገደሉ የምታነባው ለእነርሱ ብቻ አይደለም፤ አሻግራ ነገን እያየች እንጂ። የእነርሱ እውቀት አገራቸው በወቅቱ የደረሰችበት ደረጃ ላይ እንድትሆን ዘመኑን በተረዱትና በተገነዘቡት መጠን  ሚናቸውን ተጫውተዋል። ስልጣናቸውን ያለአግባብ ተጠቅመው ደሀ በድለዋል፤ ደም ግን ያን አይመልሰውም ነበር። ደም በማፍሰስ ሊመጣ የሚችልን ማስቀረትም ሆነ ያልሰሩትን ስራ መስራት እንደማይቻል ግን በወቅቱ ያሰበ ሃይል አልነበረም። ከእነርሱ እልቂት በኋላ ወታደሩ ስልጣን ሲጨብጥ መሳሪያ የያዘ ሃይልና በእውቀት ላይ መሳሪያ የጨበጠ ፋኖ እርስ በርስ መዋጋት መተላለቅም ሆነ። ኢትዮጵያ የእውቀት ማህደር የሆኑ ልጆቿን ከዚህም ከዚያም አጣች።

ነገን ያቀናሉ፣ የተስፋውን ጎዳና ይጠርጋሉ መጪውን ትውልድ ለሳይንሳዊ ምርምር፣ በእውቀት አጥምቀው  አለም ከደረሰበት ምጥቀት እንደሚያገቡት ተስፋ የተጣለባቸው ወጣቶች፣ ጎልማሶችና አዋቂዎች በጥይት አሩር ነደዱ። በአደባባይ ወንድም ወንድሙን፣ እህት እህቷን እንዲገድሉ አሊያም እንዲገደል ምክንያት ሆነ ወጣት ሲቀጠፍ የ“ፍየል ወጠጤ ልቡ ያበጠበት፣ እንዋጋ ብሎ ከነብር ላከበት” ተዘፈነ። በወቅቱ የነበሩ የእርስ በርስ ግጭቶች የብዙ ለጋ ወጣቶችን ህይወት ቀጠፈ።  እናም ያኔ የስነ ምግባር ዝቅጠት፣ የጋራ እሴቶች፣ እርስ በርስ ተማምኖ የመኖር ወግ መሸርሸር ጀመረ። እነሆ ዛሬም አላቆመም።

በደርግ ዘመን ከጭንቅና ስጋት የተላቀቀ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ አልነበረም። አባቶች  ለወንድ ልጆቻቸው ‘እያማጡ’ እናቶች መቀነታቸውን አስረው ‘እዬዬ” እያሉ ዘመናቸውን በእንባ አሳለፉ። በ1981 ዓ.ም በመንፍቅለ መንግስት ሙከራም የተሳተፉ ጄኔራሎችና ወታደሮች ህይወታቸው ተቀጠፈ። አሁንም ኢትዮጵያ ተስፋ የምታደርግባቸው ልጆቿን አጣች።

እርግማን ነው፤ ሀሳብን በሃሳብ በመሞገት ድል ከመንሳት ይልቅ ጦር ሰብቆ፣ ሳንጃ ሞሽልቆ፣ መሳሪያ ተኩሶ መንድሙን በመግደል ጀግና መባልን ከጥንት ጀምሮ የተለማመድነው ጉዳይ ነው። ሁለት ሚሊኒየም ጨርሰንና  አዲስ ጀምረንም አላቆመ። ምናልባት “ገዳይ እወዳለሁ ገዳይም አልጠላ፤ ሲደክመኝ አርፋለሁ በጎፈሬው     ጥላ” የሚለውን ግጥም እየሰማ ላደገ ማህበረሰብ ገድሎ ማጎፈር፣ ማቅራራት ለተወዳጅነት፣  ለጀግንነት ብሎም ለተመራጭነት ዋነኛ መፍትሄ አድርጎ ተቆጥሮ ይሆናል።

ከ1983 ዓ.ም በኋላም በተለያዩ ጊዜያት የሽብር ጥቃቶች ተፈጽመው ውድ ዜጎች ተሰውተዋል። በተለያየ ጊዜ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፍትሃዊነት ለማግኘት ሰዎች በየአካባቢው ጥያቄ አንስተው እንደወጡ ቀርተዋል። አሊያም አንዱ ሌላውን ትደግፋለህ ተብለው በህይወታቸው ዋጋ ከፍለዋል። የዜጎች ህይወት ጠፍቷል። ንብረት ወድሟል። ሁሉም የሚሆነው በዴሞክራሲ፣ በፍትሃዊ ተጠቀሚነት ስም እንጂ ኢትዮጵያን ወደ ቀጣይ ዘመን  ለማሻገር አቅም አጥሯቸዋል።

ዛሬም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህዝቦቻችን ይራባሉ፤ ይጠማሉ፤ ይሰደዳሉ። ዛሬም አንዱ “የራሴ ነው” ብሎ በያዘው የታሪክ ትርክት ምክንያት ሰውን ያፈናቅላል። ይገድላል። ዛሬም ህዝቦች ህልውናቸውን የሚፈትን ነገር  ይፈጸምባቸዋል። እያንዳንዱ ሰው ቢጠየቅ ሰላምን፣ ልማትንና እድገትን ይመኛል። ግን በአካባቢው ጉዳይና በትናንት ትርክት አእምሮውን ወጥሯል። ዛሬን ተሻግሮ አርቆ በማየት የህብረታችን ጥንካሬ ሊፈጥረው የሚችለውን ጸጋ መመልከት ተስኖናል። ጥቃቅን የልዩነት ትርክቶችን በመስማት እርስ በርስ የመጠላለፍ ችግር ውስጥ ገብተናል። መደማመጥ እየተሳነን በመምጣት ላይ ነው ያለነው። መግታት ይገባናል።

አገራችን ለውጥ ላይ ብትሆንም ረጋ ብሎ ከመስማትና መጪውን ዘመን ከማየት ይልቅ በአጭሩ ለመቅጨት  የሚጣደፍ ይስተዋላል። የአገር አንድነትን ሳይሆን መለያየትን ባገኘው አጋጣሚ የሚሰብክ በዝቷል። ከማያውቀው ጋር ህብረት እየፈጠረ መለየትን የሚሰብክ እየበዛ መጥቷል። ህብረት ከሚያስገኘው ጥንካሬ ይልቅ መለየት የሚያስገኘው ጥቅም በማንነት መገለጫ ስም የሚሰብክው ቁጥሩ አድጓል። ህብረት የሚያስገኘው ስነልቦናዊ፣ ቁሳዊ ሀብት፤ የጋራ እሴቶች የሚሰጡት ትሩፋትና ጸጋን ከመስበክ ይልቅ “እኛ ልዩ ነን” የሚል በቀድሞ ዘመናት የቀሩ ትርክቶች ይዞ የሚያላዝን በዝቷል። ማስተዋል ቦታዋን ትታለች፤ መከባበር ደጇ የተዘጋ ይመስላል። (እርግጥ ላለመከባበር መንስኤውን ብዙ ነው ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ) እናም መለወጥ አለብን።

የመደማመጥ ክህሎታችንን ማበልጸግ ግድ ይለናል። የማስተዋልና የማብሰልሰል አእምሯዊ ጸጋችንን ማጠንከር ዛሬ ነገ የሚባል ጉዳይ አይሆንም። አንዳችን ለሌላችን የምንተርከው ጉዳይ መሰረታዊ የጋራ እሴቶቻችን ትሩፋትና ጸጋ ላይ ያተኮሩ ማድረግ ያስፈልገናል። ለዚህ ደግሞ ራሳቸውን ለነገ የሰጡ ምሁራን፣ አዋቂዎችን፣ የአገር ሽማግሌዎችን እንሻለን። ነገን ዛሬ ለመስራት የሚታትሩ አሰላሳዮች እንፈልጋለን። ፖለቲካኛው ስልጣንን ለራሱ ከማድረግ በላይ ማሰብ ሲሳነው፣ አንዱ ሌላውን በማጥፋት ቀዳሚ መሆን ሲሻ “በቃ!!” የሚል ጠንካራ ነገን በሩቁ የሚያይ ምሁር እንሻለን። የጨለማ ዘመናችንን ለመሻገር በብርሃን ለመጥለቅለቅ ፖለቲካን ለፖለቲከኞች ትቶ በእውነትና በምክንያት የሚቆም ምሁር ግድ ይለናል።

ኢትዮጵያ እንባዋ መታበስ አለበት። በሶስት ሺህ ዘመን ውስጥ እየወደቀች እየተነሳች የገነባችው አገረ መንግስ ዳግም በጥንካሬ ታድሶ መሰራት አለበት። የጋራ እሴቶቻችንና ጸጋዎቻችንን በአዲስ መልክ እንተርክ፤ በህዝባችን አእምሮ ውስጥ በየቀኑ የሚዘሩትን እንክርዳዶች ሳያፈሩ በእውቀት እየለቀመ አዲስ የሚዘራ ዘመንን አሻጋሪ  ምሁር ይውጣ፤ የህብረት ዜማችን ዛሬም በዓለም ይናኝ።

ምክንያታዊ ትውልድን ለማፍራት ነገን ዛሬ ላይ የሚገነቡ ታላላቅ ሰዎች እንሻለን። በትናንትናው እየቆዘመ 21ኛውን ክፍለ ዘመን መግባት ያቃተው ሳንሆን ነገን ዛሬ ላይ ለመስራት የምንተጋ ትውልድ ለመሆን ጉልበታችን የታሪክ ትርክቶቻችን ማደስ ይጠበቅብናል።

ታሪካችንአርትኦት እናድርገው ሳይሆን የትናንት ቁስሉ ጠባሳችን ለዛሬ አብሮነት ማስተሳሰሪያ ገመድ እንዲሆን አድርጎ የሚተርክ ምሁር እንሻለን ማለት ነው። ጥፋትን እያገነነ፣ ትናንትን እየወቀሰ፣ በትናንት እያላዘነ “እንዲህ ነን” የሚለን ሳይሆን የምንሻው ዘመን በአዲስ ትርክት የሚያሻግረን ጠንካራ ስብእና ነው። አሁን የተጀመረውን ደግፎ የሚቆም፣ በመታደስ ውስጥ ታላቂቷን ኢትዮጵያ ለመፍጠር የሚተጋ ያስፈልገናል . . . ዛሬ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም