በሃሳብ ልዕልና የሚያምን ማህበረሰብ ለመፍጠር ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት - ምሁራን

81
ሰኔ21/2001 የሃሳብ ልዩነትን ለማስተናገድና በሃሳብ ልዕልና የሚያምን ማህበረሰብ ለመፍጠር ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ምሁራን አመለከቱ። የሃሳብ ልዕልና ላይ የሚያምን ማህበረሰብ ለመፍጠር መንግስት፣ መገናኛ ብዙሃንና ትምህርት ቤቶች የላቀ ሚና እንዳላቸውም ጠቁመዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር የሆኑት ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ የተሳሳተ ግንዛቤ በሚኖርበት ወቅት በሚቀርብ ማስረጃ መሰረት ማመን እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል። የኢትዮጵያ ህዝብ ማዕከላዊነትን የሚወድና ጽንፈኝነትን የማይፈልግ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ዳኛቸው እያቆጠቆጠ የመጣውን ጽንፈኝነት መዋጋት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በመወያየትና በመነጋገር የተለያየ አይነት አመለካከት እንዲንጸባረቅ መመቻቸት አለበት። ''በበይነ መረብ የሚጻፈው ሁሉ ጽንፍ የወጣ መሰዳደብና መወነጃጀል'' ነው ያሉት ዶክተር ዳኛቸው፤ መረጃዎችን የመፈተሽ ልማድ ባለኖሩ በሴራ የመጠለፍ ዕድል እንዳለ አመልክተዋል። በመሆኑም በመረጃ ላይ ተመስርቶ የሚቀርብን ሃሳን ለመቀበል ዝግጁ መሆን እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል። የሃሳብ ልዩነትን ለማስተናገድ በሃሳብ ከመሞገት ይልቅ በጠመንጃ ለመፍታት የሚደረገው ጥረት የሚያሳዝን መሆኑን የሚናገሩት ምሁራኑ በሃሳብ ተሟግቶ ከመግባባት ላይ ለመድረስ የሚያስችሉ ስራዎች ትኩረት ተሰጥቷቸው መከናወን እንዳለባቸው ያስገነዝባሉ። ሃሳብን የበላይ በማድረግ በሃሳብ ብቻ መነጋገር የሚቻልበት ጊዜ እንደሚመጣ እምነት እንዳላቸው ዶክተር ዳኛቸው ገልጸዋል። መጪውን ትውልድ ማስተማር፣ ባህልን መፈተሽ፣ ዴሞክራሲያዊ የሆኑ አስተሳሰቦችን ከአገሪቱ ባህልና ወግ ጋር ማስተሳሰርና ‘እኔ ብቻ ነኝ ልክ’ የሚለውን አስተሳሰብ በመተው የሌላውን ሃሳብ በሰከነ መልኩ ማዳመጥ ተገቢ እንደሆነ ያስገነዝባሉ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ዘነበ በየነ በበኩላቸው በሃሳብ የበላይነት ለመገዛት ትክክለኛ መፍትሄ ሊመጣ የሚችለው ሁሉም የድርሻውን መወጣት ሲችል እንደሆነ ያስገነዝባሉ። መንግስት፣ መገናኛ ብዙሃንና ትምህርት ቤቶች በሐሳብ ልዕልና የሚያምን ዜጋ ለመፍጠር የየራሳቸው ሃላፊነት እንዳለባቸው ጠቁመዋል። በተለይም በዩኒቨርሲቲዎች ሃሳቦች ተፋጭተው መውጣት ይጠበቅባቸዋል። ነገር ግን ከዚህ በተቃራኒ ከዩኒቨርሲቲዎች የሚሰማው ግጭት መሆኑን አስታውሰዋል። ይህ ሁኔታ መለወጥ እስካልቻለ ድረስ ከችግሩ መውጣት አዳጋች በመሆኑ መገናኛ ብዙሃን ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የኡቡንቱ አመራር ኢንስቲትዩት መስራችና ፕሬዚዳንት አቶ ዮሐንስ መዝገበ የሐሳብ የበላይነት ላይ ለማመን የመወያየት ባህልን ማዳበር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። ፖለቲከኞች የተለያየ ርዕዮተ ዓለም ቢኖራቸውን በአገር ጉዳይ ተመሳሳይ የሆነ አቋም መያዝ እንዳለባቸው አስገንዝበው፤ ''ፖለቲከኞች ለአገርና ለህዝብ ጥቅም በጋራ አብረው መስራት መቻል አለባቸው’’ ብለዋል። ፖለቲከኞቹ በሚያለያያቸው ጉዳይ ላይ በሰለጠነ መንገድ መወያየት እንደሚጠበቅባቸውም ተናግረዋል። በኢትዮጵያ በሃሳብ የበላይነት ላይ ለማመን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተጀመሩ ጥረቶች አሉ። በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አማካኝነት የሚዘጋጀው 'አዲስ ወግ' የውይይት መድረክ የሃሳብ ልዕልናን ለማስፈን የሚደረገው ጥረት አንዱ አካል ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም