በክብደት ማንሳት ሻምፒዮና የፍጻሜ ውድድሮች የደቡብ ክልል ሶስት የወርቅ ሜዳሊያ አግኝቷል

75
ሰኔ 21/2011 በ15ኛው የኢትዮጵያ ክብደት ማንሳት ሻምፒዮና ዛሬ በተካሄዱ የፍጻሜ ውድድሮች የደቡብ ክልል ሶስት የወርቅ ሜዳሊያ አግኝቷል። የክብደት ማንሳት ሻምፒዮናው ከትናንት በስቲያ በጃንሜዳ መጀመሩ ይታወቃል። በሻምፒዮናው የሶስተኛ ቀን ውሎ አራት የፍጻሜ ጨዋታዎች የተደረጉ ሲሆን ጨዋታዎቹ ትናንት በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት ወደ ዛሬ የተላለፉ ናቸው። በዚሁ መሰረት በ81 ኪሎ ግራም ወንዶች የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልሉ ተወዳዳሪ ኪሩቤል መንግስቱ የወርቅ ሜዳሊያ ተሻላሚ ሲሆን ኤርሚያስ ተስፋዬ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መስፍን ምናለ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የብርና የነሐስ ሜዳሊያ አግኝተዋል። በ73 ኪሎ ግራም ወንዶች የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደሩ ተመስገን ዜና የወርቅ ሜዳሊያ ሲያገኝ አዳነ አብጤ ከኦሮሚያ ክልል አብዱልአዚዝ ሙስጠፋ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የብርና የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል። በ64 ኪሎ ግራም ሴቶች የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልሏ ተወዳዳሪ መሰረት ሰብስቤ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ስትሆን ሽታዬ ኩመላ ከኦሮሚያ ክልል ሰሚራ ጀማል ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የብርና የነሐስ ሜዳሊያ ያገኙ ተወዳዳሪዎች ናቸው። በ59 ኪሎ ግራም ሴቶች የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልሏ ተወዳዳሪ ትንሳኤ ጋሹ የወርቅ ሜዳሊያ ህይወት ገለታው ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አይዳ ነስረዲን ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የብር እና የነሐስ ሜዳሊያ አግኝተዋል። በዚሁ መሰረት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ዛሬ ከተዘጋጁት አራት የወርቅ ሜዳሊያዎች መካከል ሶስቱን በመውሰድ የበላይነቱን ወስዷል። ዛሬ በ89 ኪሎ ግራም ወንዶች ሊካሄድ የነበረው የፍጻሜ ውድድር በጣለው ከባድ ዝናብ ወደ ነገ መተላለፉን የኢትዮጵያ ክብደት ማንሳትና የሰውነት መገንባት ፌዴሬሽን የውድድር ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ሰለሞን ዘውዱ ለኢዜአ ገልጸዋል። በክብደት ማንሳት የውድድር ህግ መሰረት ተወዳዳሪዎች ደረጃቸው የሚለየው በሁለት የአነሳስ አይነቶች እንደሆነ አቶ ሰለሞን ያስረዳሉ። የመጀመሪያው ተወዳዳሪው/ዋ ክብደቱን ከመሬት ወደ ላይ በማንሳት(ምንጨቃ snatch) እና ሁለተኛው ተወዳዳሪው/ዋ ክብደቱን በርከክ ብሎ ከመሬት በማንሳት ትከሻ ላይ ማድረግ ቀጥሎም ወደ ላይ ማንሳት (Clean and jerk) እንደሆነም ተናግረዋል። በሁለቱ የአነሳስ አይነቶች የተሻለ ነጥብ ያስመዘገበ ተወዳዳሪ አሸናፊ እንደሚሆንም አመልክተዋል። በሻምፒዮናው የትግራይ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች፣ የሐረሪ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች እንዲሁም የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች እየተሳተፉ ይገኛሉ። በወንድ 40 በሴት 25 በድምሩ 65 ተወዳዳሪዎች ተሳታፊ ሲሆኑ በወንዶች ከ55 እስከ 102 ኪሎ ግራም በሴቶች ከ45 እስከ 71 ኪሎ ግራም ውድድሮቹ የሚሳተፉባቸው የክብደት ዘርፎች ናቸው። የሻምፒዮናው አላማ በነሐሴ ወር 2011 ዓ.ም በሞሮኮ ርዕሰ መዲና ራባት በሚካሄደው 12ኛው የመላው አፍሪካ ጨዋታ የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎችን ለመምረጥ እንደሆነም ከኢትዮጵያ ክብደት ማንሳት እና ሰውነት መገንባት ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በሁለቱም ጾታዎች በሻምፒዮናው ጥሩ ተፎካካሪ የሆኑና በአፍሪካ ከሚገኙ ተወዳዳሪዎች ተቀራራቢ ውጤት ያስመዘገቡ ተወዳዳሪዎች ለመላው አፍሪካ ጨዋታ ይመረጣሉ። የአማራ፣ ሶማሌ፣ አፋር እና ጋምቤላ ክልሎች በበጀት እጥረት እና በዝግጅት ማነስ በሻምፒዮናው ላይ አልተሳተፉም። 15ኛው የኢትዮጵያ ክብደት ማንሳት ሻምፒዮና ነገ ፍጻሜውን የሚያገኝ ሲሆን በሻምፒዮናው መዝጊያ አራት የፍጻሜ ውድድሮች ይካሄዳሉ። ዛሬ በከባድ ዝናብ ወደ ነገ የተላለፈው የ89 ኪሎ ግራም ወንዶች 96 እና 102 ኪሎ ግራም ወንዶች እንዲሁም 71 ኪሎ ግራም ሴቶች የሚካሄዱት ውድድሮች ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም