ከጊዜ ወደጊዜ እየሰፋ የመጣው ያለመደማመጥ ችግር አገሪቱን ለአደጋ እየዳረጋት ነው - አስተያየት ሰጪዎች

64
ሰኔ 21/2011 ኢትዮጵያ ውስጥ ከጊዜ ወደጊዜ እየተስፋፋ የመጣው ያለመደማመጥና ያለመከባበር ችግር አገሪቱን ለአደጋ እየዳረጋት ነው ሲሉ አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተናገሩ። በመተሳሰብና መከባበር አብሮ መኖር የኢትዮጵያዊያን ለዘመናት የቆየ መገለጫ  ቢሆንም በአሁኑ ወቅት እነዚህ አገሪቱ የምትታወቅባቸው እሴቶች በመሸርሸር ላይ መሆናቸውን የማህበረሰብ ሳይንስ ምሁራን ይገልፃሉ። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአገሪቱ እየተፈጸሙ ያሉ የዜጎች መፈናቀል፣ግድያና ስርአት አልበኝነት ለዚህ መሰረታዊ ማሳያዎች መሆናቸውንም ያክላሉ። ህገ-ወጦች እየተበራከቱና የህግ የበላይነት ለአደጋ እየተጋለጠ መምጣቱ አሳሳቢ መሆኑን ብዙዎች እየገለፁት ያለ አገራዊ ችግር መሆኑም ይነገራል። ይህ ሁኔታ እየተባባሰ መጥቶ ሰሞኑን የተስተዋለው የመፈንቅለ መንግስትሙከራና የከፍተኛ መንግስት ባለስልጣናት ግድያ ደረጃ ላይ መድረሱንም እንዲሁ። ለዚህ ሁሉ ችግር ብዙ ምክንያቶች የሚገለፁ ቢሆንም በተለይ በፖለቲከኞችና ተከታዮቻቸው ዘንድ የሚታየው አለመደማመጥና አለመናበብ ዋነኛው መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው አንዳንድ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ገልፀዋል። በአሁኑ ወቅት የሚስተዋለው ይህ ሁኔታ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነም አገሪቱ ወደከፋ ችግር ውስጥ ልትገባ እንደምትችልም ነው ያስጠነቀቁት። እችናም የህግ የበላይነት እንዲመጣ መንግስት ከመቼውም ጊዜ በላይ መትጋት እንዳለበት አሳስበዋል። እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ ገለጻ ቤተሰቡን፣ አገሩንና ህዝቡን የሚያከብርና የሚጠብቅ ብሎም በማንነቱ የሚኮራ ትዉልድ ለማፍራት ሁሉም ሊሰራ ይገባል። አገር የምትለማውና የምትበለጽገው ደግሞ በመተባበርና በአንድነት በመቆም እንጂ በመጠላላትና በመጎዳዳት አይደለም ሲሉም ይናገራሉ። በመሆኑም የሰዎችን ህይወት በመቅጠፍ የሚገኝ የፖለቲካ ጥቅም እርባና ቢስ ነው የሚሉት አስተያየት ሰጪዎቹ መንግስት ይሄንን አስነዋሪ ተግባር በሚፈጽሙ አካላት ላይ ተገቢውን ህጋዊ እርምጃ መውሰድ አለበትም ብለዋል። ፖለቲካ ራሱን የቻለ ሳይንስና መርህ ያሉት ቢሆንም አሁን ላይ የሚስተዋለው ነገር ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የግል ስራውን ትቶ ወደ ፖለቲካው እየገባ ነው። ይሁንና ይህ ተግባር የፖለቲካ ትኩሳቱ እንዲያይል ከማድረጉ ባሻገር አገር እንድትለማ የማያደርግ በመሆኑ ሁሉም በተማረውና ባለው አቅምና በሚመለከተው ጉዳይ ላይ ብቻ በመስራት ለአገሩ የበኩሉን ማድረግ አለበትም ነው ያሉት። ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎችም ለዜጎች ሰላምን፣ ፍቅርንና አንድነትን በመስበክ ህዝቡ ጥላቻን አስወግዶ ሰላሙን እንዲጠብቅና እንዲተባበር ማድረግ እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም