አህጉር አቀፍ የሆቴልና ቱሪዝም አውደ- ርዕይ በአዲስ አበባ ተከፈተ

49
ሰኔ 18/2011 ከ25 ሺህ ሰው በላይ ይጎበኘዋል የተባለው ሰባተኛው የአፍሪካ የሆቴልና ቱሪዝም አውደ- ርዕይ በሚሊኒየም አዳራሽ ዛሬ ተከፈተ። በመክፈቻው ላይ የተገኙት የባህልና ቱርዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው፤ ''አውደ ርዕዩ ኢትዮጰያ በዘርፉ ያላትን እምቅ ሃብት ለአለም ለማስተዋወቅ ከፍተኛ እገዛ አለው'' ብለዋል። በኢትዮጰያ ታዳጊ ለሆነው የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የተሻለ የቴክኖሎጂ እውቀትና የልምድ ልውውጥን ለማግኘት እንደሚዳ ገልጸዋል። በአገር ውስጥ የሚካሄዱ አውደ ርዕዮች አገሪቱ ካላት እምቅ ጸጋዎች አንጻር ብዙ ያልተሰራበትን የሆቴልና የቱሪዝም ዘርፍ ለማስተዋወቅና ከዘርፉ ተዋናዮች ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ጠቀሜታቸው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል። ''ያለንን እምቅ ሃብት በመጠቀም የተሻለች ኢትዮጰያን ለትውልድ ለማስተላለፍ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች ትልቅ ሃላፊነት አለባቸው'' ያሉት ዶክተር ሂሩት በዘርፉ የተሰማሩ ሰዎች ያለውን መልካም አጋጣሚ በጥንቃቄ መጠቀም እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል። የአውደ ርዕዩ አዘጋጅና ዓለም አቀፍ የሆቴል ፕሮጀክት አማካሪ (ኦዚ) ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ቁምነገር ተከተል በበኩላቸው ዘንድሮ የተደረገው ዝግጅት ካለፉት አመታት አንጻር በብዛትና በጥራት የተሻለ መሆኑን ጠቁመዋል። የተሳታፊው ቁጥር በጥራትና በብዛት መጨመሩ በዘርፉ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለመደገፍ የሚያስችል ተግባር ለማከናወን አስተዋጽኦ እንደሚኖረው እምነታቸውን ገልጸዋል። በአውደ ርዕዩ ከ200 በላይ የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች የተሳተፉበት ይህ አውደ ርዕይ ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት ለጎብኚዎች ከፍት ይሆናል ። በመክፈቻ ስነስርዓቱ በኢትዮጵያ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የላቀ አስተዋኦ ላበረከቱ ዕውቅና ተሰጥቷል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም