የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና አህጉራዊ ሰላምና ደህንነትን ለማጠናከር ያግዛል

90
ሰኔ 20/2011የአፍሪካ አገራት ሥራ ላይ ለማዋል የወጠኑት ነፃ የንግድ ቀጠና በአህጉሪቱ ሰላምና ደህንነትን ለማጠናከር እንደሚያግዝ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሀፊ ዶክተር ቬራ ሶንግዌ ገለፁ። አፍሪካን በንግድ፣ ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ለማስተሳሰር ያለመው የአፍሪካ አህጉራዊ የንግድ ቀጠና ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። የአፍሪካውያን የእርስ በርስ የንግድ ልውውጥ፤ከአውሮፓ፣ አሜሪካና ሌሎች የዓለም ክፍሎች ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ነው። ለአብነትም የአፍሪካ አገራት 70 በመቶ የሚሆነውን መድሃኒትና የህክምና መሳሪያዎች የሚያስገቡት ከውጭ ሲሆን ለዚህም በየዓመቱ አስከ 14 ነጥብ 5 ቢሊዬን ዶላር ወጭ ያደርጋሉ። በአፍሪካ የሚገኙ የመድሃኒት አምራች ፋብሪካዎች አህጉሪቱ ከሚያስፈልጋት የመድሃኒት አጠቃላይ ምርት መሸፈን የሚችሉት ሁለት በመቶ ያህሉን ብቻ እንደሆነም መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይህንን ሚዛኑን የሳተ የንግድ ሁኔታን መቀየርን ጨምሮ የተለያዩ የምጣኔ ኃብታዊ ጥቅሞችን  ማጠናከር ይቻል ዘንድ የአህጉሪቱ አባል አገራት በመካከላቸው ነፃ የንግድ ስርዓት ለመፍጠር እንቅስቃሴ ጀምረዋል። የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና አጀንዳ 2063 በሚል በአፍሪካ ሁለንተናዊ ልማትን ለማጠናከር ታስቦ በተቀረፀው  የእድገት ውጥን ውስጥ ከተያዙት ፕሮጀክቶች ግንባር ቀደሙ ነው። ስርዓቱ በአባል አገራት መካከል ነጻ የንግድ ግንኙነትን በመፍጠር ምጣኔ ኃብታዊ ውህደት ያመጣል ተብሎ የታመነበት ስርዓቱ አጠቃላይ ዓመታዊ የምርት መጠናቸው 3.4 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ 1.2 ቢሊዮን ሸማቾች ይኖሩታል። ይህም በአገራቱ ጠንካራ ምጣኔ ኃብት ለመገንባት እንደሚያስችል፤ በዚህም ሳቢያ አህጉራዊ ሰላምና መረጋጋት እንደሚጠናከር ነው የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሀፊ ዶክተር ቬራ ሶንግዌ አፍሪካን በንግድ፣ ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ለማስተሳሰር ያለመው የአፍሪካ አህጉራዊ የንግድ ቀጠና ፎረም በአዲስ አበባ ዛሬ ሲጀመር የተናገሩት። ነጻ የንግድ ቀጠናው እውን መሆን በአህጉሪቱ የሚኖሩ ዜጎችን አንድነትና ትብብር በማጎልበት በልማት፣ በሰላምና ጽጥታ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመምከር ያስችላል ብለዋል። የኢፌደሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ከፍተኛ የፖሊሲ አማካሪ አቶ ማሞ ምህረቱ በበኩቸው ጠንካራ የንግድ ትስስር መፍጠር አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን በር ይከፍታል ሲሉ የዋና ፀሃፊውን ሀሳብ አጠናክረዋል። የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና አገሮችን በበቂ ሁኔታ በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ በማስተሳሰር ሰላማቸውን በጋራ እንዲጠብቁ ያደርጋል ነው ያሉት አቶ ማሞ ። ይሁን እንጂ እስካሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በአፍሪካውያን መካከል በቂ የንግድ፣ ኢንቨስትመንትና አጠቃላይ የኢኮኖሚ ትስስር ባለመኖሩ አስተማማኝ ሰላም ማስፈን አልተቻለም ብለዋል። ኢትዮጵያ ከውጭ ከምታስገባው አጠቃላይ ምርት መካከል ከአፍሪካ አገሮች የሚመጡት 4 በመቶ ብቻ  መሆናቸውን በመግለጽ። "ይህ ደግሞ የኢኮኖሚ ትስስሩ ደካማ መሆኑን ከማሳየቱም ባለፈ በሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ላይ ተቀራርበን አለመስራታችንን ያሳያል" ብለዋል። በአህጉሪቱ ጠንካራ የንግድ ትስስር መፍጠር ከተቻለ በቀጠናው ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ጉልህ ሚና እንደሚኖረውም አመልክተዋል። ጥንካራ የንግድና ኢኮኖሚ ትሰስር መፍጠር በረጅም ጊዜ አስተማማኝ ሰላም ያመጣል፤ በዚህ ላይ ደግሞ ጠንክሮ መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል። በመሆኑም የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠናውን ጠንካራ መሰረት ላይ በመገንባት አህጉራዊ ሰላምና ጸጥታን ማስፈን እንችላለን ብለዋል። በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ቀንድ ዋና ጸሃፊ ልዩ መልዕክተኛ ፓርፌት ኦናንጋ በበኩላቸው ሰላምና ጸጥታ ከሁሉም ይቅደም ይላሉ። የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ውጤታማ መሆን የሚችለው በቀጠናው ሰላምና መረጋጋት ሲሰፍን መሆኑን በመግለጽ። ባለፈው መጋቢት 12 ቀን 2011 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው የአፍሪካ አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት 52 አገሮች ሲፈርሙት 21 አገራት ደግሞ በየአገሮቻቸው ምክር ቤት አጽድውታል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም