ወጣቱ በአሉባልታ ወሬ ሳይታለል ክልሉንና ሀገሪቱን ለመበታተን የሚጥሩ አካላትን መታገል አለበት....የባህር ዳር ከተማ ወጣቶች

60
ባህር ዳር ሰኔ 19/2011 የአማራ ክልል ወጣት በአሉባልታ ወሬ ሳይታለል የራሱን አቋም በመያዝ ክልሉንና ሀገሪቱን ለመበታተን እየተጉ ያሉ አካላትን መታገል እንዳለበት የባህር ዳር ከተማ ወጣቶች ገለጹ። ባለፈው ቅዳሜ በደረሰባቸው ጥቃት ውድ ሕይወታቸው በተሰዋው የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የቀብር ሥነስርአት ላይ የተገኙ ወጣቶች ለኢዜአ እንዳሉት ወጣቱ ነገሮችን በስሜት ሳይሆን በአስተውሎት ሊያጤን የሚገባው ወሳኝ ወቅት ላይ ነው። ክልሉን የጦርነት ቀጠና ለማድረግ የሚተጋ ቡድንም ሆነ ግለሰብ የአማራ ክልል ጠላት እንጂ ወዳጅ ሊሆን ስለማይችል ወጣቱ በክልሉ እየተነዙ ካሉ የውሸት ወሬዎች እራሱን በማራቅ ክልሉን የጦርነት ቀጠና ከመሆን ሊታደግ እንደሚገባም አመልክተዋል። ወጣት ወርቁ ምንያህል እንደገለጸው ወጣቱ በአሉባልታ ወሬ ሳይበረዝ በራሱ አቋም ጸንቶ ክልሉንና ሀገሪቱን ለማፈራረስ የሚጥሩ የጥፋት ኃይሎችን በጋራ መታገል ይኖርበታል ። የክልሉና የሀገር ባለውለታዎች በደረሰባቸው ጥቃት ሕይወታቸውን ማጣታቸው አስደንጋጭ ቢሆንም ለክልሉና ለሀገሪቱ ህዝብ የጋራ ጥቅም የሚሰሩ በርካቶች ስላሉ መደናገጥ እንደማያስፈልግ ተናግሯል ። “ብዙ መስራት የሚችሉ አመራሮቹን በመስዋዕትነት ብናጣም ክልሉን ከእነሱ ውጪ ሰው እንደሌለ ለማስመሰል የሚነዛ ወሬ አግባብ አይደለም” ያለው ወጣቱ፣  ሕብረተሰቡ በተለይ ወጣቱ ለእዚህ ትኩረት ሳይሰጥ በቀጣይ ከሚተኩ አመራሮች ጋር በመስራት ክልሉን ከመበታተን ሊታደግ እንደሚገባ አመልክቷል ። የክልሉንና የሀገሪቱን ህዝብ የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይጥሩ የነበሩ ከፍተኛ አመራሮች ያነገቡትን ሀገራዊ ራዕይና የጀመሩትን ሥራ ለማስቀጠል ወጣቱ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ አለበት ያለው ደግሞ ወጣት አንተነህ ተናኜ ነው። “ወጣቱ የሀሳብ ልዩነት ቢኖረውም በክልሉ አንድነት ላይ መደራደር የለበትም፤ ለራሳቸው የግል ፖለቲካ ትርፍ ሲሉ ሊከፋፍሉት የሚሞክሩ ኃይሎችን የውሸት ወሬ በጋራ መቃወም አለበት” ብሏል ። የሐሳብ ልዩነት ሊስተናገድ የሚችለው በቀድሚያ ክልሉ በፖለቲካና በኢኮኖሚ ተጠናክሮ ሲገኝ ብቻ መሆኑንም ተናግሯል ። ወጣቱ ክልሉን ለማፈራረስ የሚተጉ የጥፋት ኃይሎችን በጋራ መታገል እንዳለበትም ነው ወጣት አንተነህ የገለጸው። “በክልሉ የተፈጠረው አስነዋሪና አሳፋሪ ተግባር ወጣቱ ግለሰቦችንም ሆነ ቡድኖችን በወሬ ከማመን እንዲቆጠብ የሚያስተምር ነው” ያለው ሌላኛው የከተማው ነዋሪ ወጣት ደሴ ይንገስ ነው። “የምናምናቸውና የምንመካባቸው ሰዎች የማይጠበቅባቸውን ድርጊት መፈፀማቸው ከዚህ በኋላ ነገሮችን በምክንያት ለመደገፍና ለመቃወም ያግዘናል “ ብሏል። ዛሬ በባህር ዳር ከተማ በተፈፀመው የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የቀበር ሥነሥርአት ላይ የሱዳንና የኤርትራ ልዑካንን ጨምሮ ከፍተኛ የክልሉና የፌዴራል የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም