የተፈጸመው ጥቃት ለሀገራዊ ለውጡ ቀጣይነት የበለጠ የሚያነሳሳ እንጂ ወደኋላ የሚያስብል አይደለም…የሌሞ ወረዳና ሆሳዕና ከተማ ነዋሪዎች

65

ሆሳእና ሰኔ 19/2011 በአማራ ክልልና በመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሮች ላይ የተፈጸመው ጥቃት ለሀገራዊ ለውጡ ቀጣይነት የበለጠ የሚያነሳሳ እንጂ ወደኋላ የሚያስብል አይደለም ሲሉ በሀዲያ ዞን የሌሞ ወረዳና ሆሳዕና ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

በሆሳዕና ከተማ ቤቴል ቀበሌ የሚኖሩት አቶ አማን ኑሬቦ ለኢዜአ እንደገለጹት በወገኖቻቸው ላይ የተፈፀመው ጥቃት እጅግ አሳዛኝና አንገት የሚያስደፋ ተግባር ነው።

“የተፈጸመው የጥፋት ድርጊት ሀገሪቱ ሊተኩ የማይችሉ ውድ ልጆቿን እንድታጣ አድርጓታል” ብለዋል።

በጥቃቱ መስዋዕትነት የከፈሉ ከፍተኛ አመራሮች አደራቸውንና የጀመሯቸውን ስራዎች በማስቀጠል ሀገሪቱን ወደተሻለ ደረጃ ላይ ማድረስ የቀሪው ትውልድ ግዴታ መሆኑንም አመልክተዋል።

የተፈፀመው የጥፋት ተግባር የሀገሪቱን ልማት ለማደናቀፍ መሆኑን የገለጹት አቶ አማን ጥቃቱ ወደኋላ የሚያስብል ሳይሆን የሀገሪቱን ለውጥ በጋራ ለማስቀጠል ለህብረተሰቡ ብርታት እንደሚሆን ተናግረዋል።

“በሀገር መከላከያ ሠራዊትና በአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ላይ የተፈፀመው ግድያ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ የተጀመረውን ልማት አያደናቅፍም” ሲሉ የተናገሩት ደግሞ በሀዲያ ዞን ሌሞ ወረዳ ሊሳና ሴና ቀበሌ ነዋሪ አቶ ታገሰ አበበ ናቸው።

ህብረተሰቡ በተፈጠረው ክስተት መደናገጥ እንደሌለበት ገልጸው፣ “ክስተቱ ሀገራዊ ልማትንና ሰላም እንዳይመጣ የማይፈልጉ አካላት እንዳሉ አመላካች ነው” ብለዋል።

በተፈጸመው ድርጊት በእጅጉ ማዘናቸውንና የሚወገዝ ተግባር መሆኑን የገለጹት አቶ ታገሰ፣ ለሀገርና ለህዘብ ሰላም ሲባል ለሰላም ዘብ መቆም እንደሚገባ አመልክተዋል።

በሆሳዕና ከተማ አራዳ ቀበሌ የሚኖሩት ወይዘሮ ገነት ዮሐንስ በበኩላቸው “ድርጊቱ ሀገራዊ ለውጡን ሆን ብሎ ለማደፍረስ የተሸረበ ሴራ “ ነው ብለዋል።

በጥቃቱ ሀገራዊ ለወጡን የሚያስቀጥሉና ልማትን የሚያፋጥኑ መሪዎች መስዋዕት በመሆናቸው በእጅጉ ማዘናቸውን ገልጸዋል።

በክስተቱ የሀገሪቱ የሰላም፣ የመቻቻልና የአንድነት ጉዞ ወደ ኋላ ከመጎተት ይልቅ ሂደቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያነሳሳ መሆኑንም ወይዘሮ ገነት ተናግረዋል።