ለህዝብ ጥቅም ሲታገሉ ያለፉ አመራሮችን ዓላማ ማሳካት ይገባል… በባህርዳር የተገኙ የስርዓተ ቀብሩ ተሳታፊዎች

43
ሰኔ 19/2011 ለህዝብ ጥቅም መከበር ሲታገሉ የተሰዉ አመራሮችን ዓላማ ከግብ በማድረስ ሰማዕታቱን መካስ ይገባል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የቀብር ሥነ-ስርዓቱ ተሳታፊዎች ገለጹ። ዛሬ በተከናወነው የማቾቹ አመራሮች የቀብር ስነ-ስርዓት ላይ የተገኙት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ናትናኤል ተሻለ እንዳሉት ክስተቱ ወንድም ወንድሙን ተኩሶ በመግደል የተፈፀመ አሳዛኝ ድርጊት ነው። ይህም የክልልና ሀገር አቀፍ ለውጡን በማደናቀፍ የተረጋጋ ሰላምና ዘላቂ ልማት እንዳይረጋገጥ እንዲሁም የህዝቡ የረጅም ጊዜ ጥያቄ እንዳይመለስ አልሞ የተፈፀመ አስነዋሪ ተግባር እንደሆነ ተናግረዋል። “አመራሮቹ ለለውጡ ውጤታማነትና ለህዝብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ሲታገሉ በህዝብ ስም የተሰዉ ጀግኖች በመሆናቸው የሞቱለት ዓላማ እንዲሳካ በጋራ መረባረብ ይገባል” ብለዋል። በነዚህ አመራሮች ህልፈተ-ህይወት ምክንያት ሊፈጠር የሚችለውን የአመራር ክፍተት በመተጋገዝና በመታገስ ሰላሙ የተረጋጋና አንድነቱ የጠነከረ ክልል ለመፍጠር በፅናት መታገል እንደሚገባም አስረድተዋል። የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ባለው ባዬ በበኩላቸው ድርጊቱ ሁሉንም የሚያስቆጭ የእርስ በእርስ ጥቃት ነው። “የአመራሮች ዓላማ ከግብ እንዲደርስና የታገሉለትና የለፉለት ህዝብ እርካታ እንዲያገኝ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ አንድነት ጠንክሮ መስራት የግድ የሚልበት ወቅት ነው”ብለዋል። ወጣቱ አመራሮች የሞቱለትን ዓላማ በመረዳት ጉልበቱን ሳይሰስት ከስሜታዊነት በመውጣት በአንድነት ለክልሉ ዘላቂ ልማትና ሰላም መስራት እንዳለበትም አብራርተዋል። በየደረጃው ያለው አመራርም በየቦታው እየተቀጠፈ ያለው የክልሉ ልጆች ህይወት ሊያሳስበው እንደሚገባ ጠቁመው ጠንካራ አንድነት ፈጥሮ ችግሩ እልባት እንዲያገኝ ህዝብን አቅፎ ሊሰራ እንደሚገባ አመልክተዋል። “የአማራን ህዝብ ሊጠቅሙ የሚችሉ አመራሮች በመሞታቸው ብቻ ማዘንና መተከዝ ሳይሆን ለአላማቸው መሳካት መስዋዕትነት ጭምር መክፈል ይገባል” ያሉት ደግሞ ከጎንደር ከተማ የመጡት አቶ ተስፋ ታምራት ናቸው። የተጀመረው የሰላምና የልማት እንዱሁም የለውጥና የነፃነት ትግል ረጅምና እልህ አስጨራሽ በመሆኑ በፅናትና በትጋት በመስራት ግቡን እንዲመታ በተደራጀ አግባብ መስራት ይገባል”ብለዋል። በሥርአተ-ቀብሩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንንና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳረጋቸውን ጨምሮ የክልሎች ርዕሳነ-መስተዳደሮች ፣ከፍተኛ አመራሮች የሱዳንና የኤርትራ የልኡካን ቡድን አባላት የባህርዳርና አካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም