''ሞት የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ክስተት ቢሆንም በእንዲህ አይነት ጭካኔ ሲፈጸም እጅግ መሪር ነው''- ም/ጠ/ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን

171
ሰኔ 19/2011 ''ሞት የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ክስተት ቢሆንም በእንዲህ አይነት ክህደትን በተላበሰና በከፋ ጭካኔ ሲፈጸም እጅግ መሪር ነው'' ሲሉ ነው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የገለጹት። አቶ ደመቀ በአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች የአስከሬን ሽኝት ስነ-ርስዓት ላይ በሲቃ የታጀበ ንግግር አድርገዋል። ድርጊቱ ሲፈጸም ለስራ ጉዳይ ከአገር ውጭ እንደነበሩ ያስታወሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እዚያው እያሉ በሰሙት ነገር ከፍተኛ ድንጋጤና ሀዘን እንደተሰማቸው ገልጸው፣ ዶክተር አምባቸው፣ አቶ እዘዝን ና አቶ ምግባሩን ከአገር ከመውጣታቸው በፊት ስለ ቀጣይ ስራዎቻቸው በስልክ አነጋግረዋቸው እንደነበር ገልጸዋል። ''ሰው ባሰበው አይውልምና ያልተጠበቀው ሆነ'' ያሉት አቶ ደመቀ ድርጊቱ እጅግ አሳዛኝና ጭካኔ የተሞላበት ነው ብለዋል። “ልጅነታቸውን ሳይጨርሱ ለህዝብ አገልግሎት ህይወታቸውንና ማህበራዊ መስተጋብራቸውን በመስጠት ለለውጡ ከባድ ዋጋ ከፍለው ለብዙዎች ነጻነትን ካወጁና ለመጪው ዘመን ብርቱ ክንድ ሆነው በተሰለፉ የለውጥ ዘዋሪዎች ላይ እንዲህ አይነት ድርጊት መፈጸሙ ውስጥን የሚያደማ ነው" ሲሉ ተናግረዋል። ''በእስር ቤት ያሉ ዜጎቻችን ተስፋቸው ጨልሟል፣ አካላቸው ጎድሏል፣ የህሊና እስረኛ ሆነዋል ብለው በግንባር ቀደምትነት ለታገሉ መሪዎች ምላሹ ጥይት መሆኑ ከክህደትና ከእናት ጡት ነካሽነት ውጪ ሌላ ምን ሊባል ይችላል'' ነው ያሉት። በአገር አቀፍና ለክልል አቀፍ ተልዕኮ መሳካት በስራ ላይ እያሉ ህይወታቸውን ላጡ የመከላከያ ሰራዊት አመራሮችና የአዴፓ አመራሮች ህልፈት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልጸዋል። ጥቃቱ በህይወትና ማህበራዊ ገጽታው ለተጎጂዎችና ለቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ለትግል አጋሮቻቸው እጅግ የከበደ ከመሆኑ ባለፈ የህዝብን ታሪክ የማይመጥን አረመኔያዊ ድርጊት መሆኑንም ነው የገለጹት። የድርጊቱን መፈጸም ተከትሎ በባህርዳርና አካባቢዋ ከዚህ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ ና በቁጥጥር ስር እንዲውል ርብርብ ላደረጉት የክልሉ ነዋሪዎች፣ የጸጥታ አካላትና ልዩ ልዩ የመንግስት አካላት ምስጋና አቅርበዋል። ለሟች ቤተሰቦች፣ ለክልሉ ነዋሪዎችና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መጽናናትን ተመኝተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም