በኦሮሚያና በአዲስ አበባ በኮሌራ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ጨምሯል - የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት

87
አዲስ አበባ ሰኔ 19/2011 በአብዛኞቹ ክልሎች ተከስቶ የነበረው የኮሌራ ወረርሽኝ ባለበት የተገታ ቢሆንም በኦሮሚያ ክልልና በአዲስ አበባ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ። ኢንስቲትዩቱ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ጎዳና ላይ ለሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የኮሌራ ወረርሽኝ ክትባት ለመስጠት መዘጋጀቱንም ገልጿል። የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ቶሌራ ለኢዜአ በላኩት መግለጫ እንዳስታወቁት በአማራ፣ በትግራይ፣ በሱማሌ ክልሎችና በድሬዳዋ መስተዳድር ተከስቶ የነበረውን የኮሌራ ወረርሽኝ ባለበት የመግታት ሥራ ተከናውኗል። በአንፃሩ በኦሮሚያ 38፣ በአዲስ አበባ 31 ተጨማሪ ሰዎች በወረርሽኙ መያዛቸውንና በበሽታው የተያዙት ሰዎች ቁጥርም ወደ 702 ማሻቀቡን ገልጸዋል። በአማራ ክልል 202 ሰዎች በኮሌራ ወረርሽኝ ተይዘው የነበረ ቢሆንም ባለፉት 25 ቀናት አዲስ በሽተኛ አለመኖሩ ተመልክቷል። በተመሳሳይ በሱማሌ ክልል ባለፉት 31 ቀናት፣ በትግራይ ባለፉት 14 ቀናት እንዲሁም በድሬደዋ ባለፉት ስምንት ቀናት አዲስ ህመምተኛ አለመገኘቱን መግለጫው ያመለክታል። ወረርሽኙ በተከሰተባቸው ክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች በበሽታው የተያዙ ሰዎችን ማከም የሚያስችሉ 22 ለይቶ ማከሚያ ማዕከላት መወቋቋሙና፤ ከፍተኛ ተጋላጭነት ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች የመለየት ሥራም መሰራቱን ጠቅሰዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሐረርጌ ዞን ለወረርሽኙ ተጋላጭ ናቸው ተብለው ለተለዩ 291 የኅብረተሰብ ክፍሎች ክትባት መስጠት እንደሚጀመር በመግለጫው ተመልክቷል። በተጨማሪም ወረርሽኙ በተከሰተባቸው ክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች ኑሯቸውን በጎዳና ላይ ላደረጉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ክትባት መስጠት እንደሚጀመር የምክትል ዋና ዳይሬክተሩ መግለጫ ያስረዳል። እስካሁን በበሽታው የተያዙ 16 ሰዎች መሞታቸው የተረጋገጠ ሲሆን፤ ወረርሽኙን ለመግታት ባለፉት ሳምንታት በመጀመሪያ ዙር ለ17 ሺህ የወረርሽኙ ተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎች ክትባት መሰጠቱ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም