በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሕብረተሰቡ በሰላም ማስጠበቅ ሥራ ተሳትፎውን እንዲያጠናክር ተጠየቀ

92
አሶሳ ሰኔ 19/2011 በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰላምን ለማስጠበቅ እየተደረገ ላለው ጥረት ሕብረተሰቡ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ ። በአሶሳ ከተማ በግለሰቦችና በተደራጁ ቡድኖች እየተፈፀሙ ያሉ የወንጀል ድርጊቶችን ማስቆም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ትናንት የምክክር መድረክተካሂዷል። የክልሉ ፖሊስ ኮሚሸን ኮሚሽነር መሀመድ አሚደሚል በመድረኩ ላይ እንደገለፁት በከተማው በቀንና በምሽት የሚፈፀሙ የዘረፋና የስርቆት ወንጀሎች እየተበራከቱ ነው ። “የግለሰቦች ቤት በየጊዜው እየተሰበረ ዘረፋ እየተካሄደ ነው” ያሉት ኮሚሽነሩ ከተማው የህገ-ወጦች መሸጋገርያ እየሆነ መምጣቱንም ተናግረዋል ። በግለሰቦች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ፅንፈኛ ቡድኖች ወደ ብሔር ግጭት ለመለወጥ እንደሚጥሩም ጠቁመዋል። ፓሊስ ወንጀለኞችን ለመያዝ በሚያደርገው ጥረት በቡድን ከተደራጁ ኃይሎች ጥቃት እየተፈፀመበት መሆኑንም ኮሚሽነር መሀመድ ተናግረዋል። “አንዳንድ ነዋሪዎች ማንነታቸው ላልታወቁ ሰዎች ቤት በማከራየት ችግሩን ሲያባብሱ ይስተዋላል” ያሉት ኮሚሽነሩ ተደራጅተው የፀጥታ ኃይሉን እንቅስቃሴ ለሚያውኩ ቡድኖች ምሸግ የሚሆኑበት አጋጣሚ መኖሩንም ጠቅሰዋል። ፖሊስ በወንጀል ድርጊቱ የተሰማሩ ግለሰቦችና ቡድኖችን በቁጥጥር ስር በማዋል ለህግ እያቀረበ በመሆኑ ሕብረተሰቡ ድርጊቱን ለማስቆም የበኩሉን እገዛ እንዲያደርግም ጠይቀዋል። ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ አሸብር በላይ በሰጡት አስተያየት በፓሊስና በነዋሪዎች መካከል ያለው የቅንጅት መላላት ለወንጀል መበራከት ምክንያት መሆኑንም ተናግረዋል ። “ፖሊስ ብቻውን የሚፈለገውን ሰላም አያመጣም”ያሉት አቶ አሸብር ከዚህ ቀደም በወጣቶች ይደረግ የነበረው የአካባቢን ሰላም የማስጠበቅ ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አመላክተዋል። የአሶሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ሁመር መሐመድ በበኩላቸው “በከተማው እየተስተዋለ ያለው የወንጀል ድርጊትና የሰላም እጦት እንዲቆም ህብረተሰቡንያሳተፉ የመከላከል ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ “ ብለዋል ። በአሶሳ ከተማ ከ60ሺህ በላይ ነዋሪዎች እንደሚኖሩ መረጃዎች ያሳያሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም