በምዕራብ ኦሮሚያ 'በህዝብ ስም ጫካ ገብቻለሁ' የሚለው ቡድን እንደማይወክላቸው ነዋሪዎች ገለጹ

53
አዲስ አበባ ሰኔ 19/2011 የኦሮሞን ህዝብ በመወከል "ጫካ ገብቻለሁ" የሚለው ቡድን እንደማይወክላቸው በምዕራብ ኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች ነዋሪዎች ለተቃውሞ ሰልፍ በመውጣት ገለጹ። የቄለም ወለጋ፣ የምዕራብና ምስራቅ ወለጋ እንዲሁም ቡኖ በደሌ የተለያዩ ወረዳዎች ነዋሪዎቹ ''የኦሮሞን ህዝብ ነጻ አወጣለሁ'' በማለት ጫካ የገባ ማንኛውም ቡድን እንደማይወክላቸው ትናንት ባካሄዱት የተቃውሞ ሰልፉ ላይ ባሰሙት መፈክርም አረጋግጠዋል። ነዋሪዎቹ እንደገለጹት፤ ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት በመሆኑ ሰላምን የማረጋገጥ ስራ መከናወን አለበት። ሰላም ከሌለ ልማትም ሆነ ሌሎች ነገሮች የማይረጋገጡ በመሆኑ ሰላምን ለማስፈን ከለውጡ ሃይል ጋር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል። መንግስት ነገሮችን በሆደ ሰፊነት መያዙን ያደነቁት ሰልፈኞቹ ከህዝብ ፍላጎት አፈንግጠው በህገወጥ ድርጊት ውስጥ የሚሳተፉ አካላት ላይ እርምጃ በመውሰድ የህግ የበላይነትን እንዲያረጋግጥ ጠይቀዋል። ሰውን መደብደብና መግደል ክፉ የሆነ ተግባር መሆኑን በመግለጽ ያወገዙት ሰልፈኞቹ አለመግባባትን በሃይል ሳይሆን በመነጋገር መፍታት እንደሚቻል ጠቁመዋል። የተቃውሞ ሰልፍ በመውጣት በወገኖቻቸው ላይ እየደረሰ ያለውን ግድያ ያወገዙት የምዕራብ ኦሮሚያ ነዋሪዎች፤ በመንግስትና በኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) መካከል ስምምነት ተደርጎ በመግባባት የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ጠቁመዋል። ሆኖም ኦነግ ሸኔ በሚል ጫካ የገባ ሃይል እየደበደበ፣ እየገደለ በህዝቡ ላይ ሽብር ፈጥሯል። በአሁኑ ወቅት በመንግስትና በኦነግ መካከል ስምምነት ላይ የተደረሰ ቢሆንም በህዝብ ስም ጫካ የገባ ቡድን የኦሮሞን ህዝብ እንደማይወክል ገልጸዋል። ''በኦነግ ስም ዛሬ በጫካ ውሰጥ በኦነግ ሸኔ ስም ህዝቡ እየተዘረፈ ይገኛል።'' ያሉት ነዋሪዎች ከህዝብ ፍላጎት ተቃራኒ የሆነ ድርጊት በመፈጸም ላይ እንደሆነ አመልክተው ድርጊቱ እንዲቆም ጠይቀዋል። ነዋሪዎቹ የአካባቢያቸውን ሰላም ለማረጋገጥ የድርሻቸውን ለመወጣት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል። ሰላም ከሌለ ምንም ዓይነት ነገር ማካሄድ የማይቻል በመሆኑ የአካባቢያቸውን ሰላም ለማረጋገጥ ከመንግስትም ሆነ ከሌሎች ለሰላም ከሚሰሩ ሃይሎች ጋር በመተባበር እንደሚሰሩ ገልጸዋል። “ሸኔ” ተብሎ በሚጠራው ታጣቂ ቡድን የአካባቢያቸው መረጋጋት ባለመፈጠሩ ሰው ወጥቶ መግባት እንዳልቻለ ተናግረው፤ በየደረጃው የሚገኙ አመራር አባላት እንደሚታገቱና እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ጠቁመዋል። የአመራር አባላት መታገትና መገደል የመንግስት ስራ በአግባቡ እንዳይሰራ እንቅፋት መሆኑን በመግለጽ የሁኔታውን አስቸጋሪነት አስረድተዋል። ለዚህም ህዝብና መንግስት ተቀናጅተው መታገል እንደሚገባቸው ነው የተገለጸው። ግንቦት 21 ቀን 2011 ዓ.ም ኦነግ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት እና እርቀሰላም ኮሚቴ ጋር በሰጠው መግለጫ፤ የታጠቀ ሰራዊት እንደሌለው አረጋግጧል። ኦነግ አገሪቷ በለውጥ ሂደት ውስጥ በገባችበት ወቅት ሁሉም ተቃዋሚ ሀይሎች በሰላማዊ መንገድ መታገል እንደሚችል ተገልጾ በመንግስት ጥሪ ከተደረገ በኋላ ወደ አገር ቤት መመለሱ ይታወሳል። በተያያዘም ሰልፈኞቹ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና በአዲስ አበባ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ላይ የተፈጸመውን ግድያ አውግዘው ድርጊቱ በአገሪቱ የመጣውን ለውጥ ለመቀልበስ የተደረገ ሙከራ በመሆኑ አጥብቀው እንደሚቃወሙት ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም