የጉባኤው የበላይ ጠባቂዎች የሟች ቤተሰቦችን አጽናኑ

117
ሰኔ 17/2011 የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የዶክተር አምባቸው መኮንንና የሜጄር ጄኔራል ሰዓረ መኮንን ቤተሰቦች መኖሪያ ቤት በመሄድ አጽናንተዋል። የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር አምባቸው መኮንን ና የአደረጃጀት አማካሪያቸው አቶ እዘዝ ዋሴ እንዲሁም ሜጄር ጄነራል ሰዓረ መኮንንና ሜጀር ጄነራል  ገዛኢ አበራ  በደረሰባቸው ጥቃት ህይወታቸው ማለፉ ይታወቃል። የሃይማኖት አባቶቹ ዛሬ ጠዋት አዲስ አበባ በሚገኘው የዶክተር አምባቸው መኮንንና  የሜጄር ጄኔራል  ሰዓረ መኮንን  ቤተሰቦች ቤት በመገኘትአጽናንተዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሊቀ-ጳጳስ ብጹዕ ወቅዱስ  አቡነ  ማቲያስ  "ወንድም ወንድሙን  ገድሎ ከጸጸት ባለፈ የሚጠቀመው ነገርየለም" ነው ያሉት። ችግሮችን በውይይትና በንግግር መፍታት እየተቻለ ንጹሃንን  ገድሎ ፍላጎትን  ለማሟላት  መሞከር  ተገቢ አይደለም ብለዋል። ፈጣሪ የፈጠረውን ነፍስ ማጥፋት በየትኛውም  ሃይማኖት የተወገዘ በመሆኑ  ማንኛውም  ሰው  ድርጊቱን ማውገዝ እንዳለበትም ተናግረዋል። በአመራሮቹ ላይ የተፈጸመው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት የሟች  ቤተሰቦች ብቻ  ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያ ሀዘን መሆኑንም ፓርቲያርኩ ገልጸዋል። ሰው የተፈጠረው ለሞት ቢሆንም ከፍተኛ መስዕዋትነትን  እየከፈሉ  አገራቸውን  ወደ  ተሻለ  ደረጃ  ለማድረስ  ጥረት  በማድረግ ላይ ያሉ ሰዎች  ላይ ድርጊቱመፈጸሙ  ሀዘኑን የከፋ እንደሚያደርገውም አቡነ ማቲያስ ተናግረዋል። ሀዘን ማብዛት ጉዳቱ የከፋ በመሆኑ የሟች ቤተሰቦች ከሃዘናቸው  እንዲጽናኑም  ነው  የመከሩት። የኢትዮጵያ  የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ  በአመራሮቹ  ላይ የደረሰውን  ጥቃት አስመልክቶ  ትናንት በሰጠው  መግለጫ ባለ 10 ነጥብ የአቋም  መግለጫ በማውጣት  ድርጊቱን ማውገዙ ይታወቃል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም