ለምርትና አገልግሎት ዓለም አቀፍ ዕውቅና የሚያሰጡ ተቋማት ቁጥር አነስተኛ ነው

74
አዲስ አበባ ሰኔ 2/2010 ለምርትና አገልግሎታቸው ዓለም አቀፍ ዕውቅና የሚያሰጡ ተቋማት ቁጥር አነስተኛ መሆኑን የብሔራዊ አክሪዲቴሽን ጽህፈት ቤት አስታወቀ። የአክሪዲቴሽን ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ ለስምንተኛ፤ በዓለም አቀፍ ደግሞ ለ13 ጊዜ "አክሪዲቴሽን ደህንነቱ ለተጠበቀ ዓለም’’ በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ነው። የጽህፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ አርአያ ፍስሐ እንዳሉት ተቋማት ምርትና አገልግሎታቸውን፣ የመጠቀሚያ መሳሪያዎቻቸውንና ባለሙያዎቻቸውን ዓለም አቀፍ ዕውቅና ለማሰጠት ያላቸው ተነሳሽነታቸው ዝቅተኛ ነው። የተቋማት ዕውቅና ማግኘት ኢንቨስትመንትን ለማሳብና የአገሪቱን ኢኮኖሚ ሊያሳድጉ የሚችሉ አማራጮችን ለማስፋት ያስችላል ብለዋል። ጥቅም ላይ የሚውሉ የቤተ-ሙከራ መሳሪያዎችና ምግብ ደህንነቱ ሳይረጋገጥ ለህብረተሰቡ ማቅረብ የሰውን ጤና ስለሚጎዳ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል። ለዚህም እንደ ምክንያትነት የጠቀሱት በመንግስት በኩል የአክሪዲቴሽን አገልግሎት አስገዳጅ ህግ አለመኖርን ነው። ተቋማትና ግለሰቦች ዓለም አቀፍ ዕውቅና ሲሰጣቸው የገበያ ተወዳደሪነታቸው ይጨምራል፣ ምርትና ምርታማነት ያድጋል፣ የህብረተሰቡን ጤናና ደህንነትም ማረጋገጥ እንደሚቻል ጠቅሰው ህብረተሰቡም ያለስጋት አገልግሎቱን ያገኛል ነው ያሉት። ስለዚህ ተቋማት መስፈርቶቻቸውን አሟልተው ዓለም አቀፍ ዕውቅና እንዲያገኙ ተቆጣጣሪ ተቋማት ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል። በኢትዮጵያ የምግብ፣ መድሃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን የምግብ ጥራት ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ስዩም ወልዴ እንዳሉት የምግብ ደህንነትን ለማረጋገጥ ከአምራቹ እስከ ፋብሪካ መስፈርቱን ማሟላት ይገባል። በተለይም ለምርት ማሳደጊያነት የሚውል ኬሚካል መጠን አለመታወቅ፣ ከምርት በኋላ ጥቅም ላይ የሚውሉ መሳሪዎች ጥራት ማነስና ምርቶች የሚቀመጡበት ቦታ መስፈርቱን ያሟላ አለመሆን የህብረተሰቡን ጤና ይጎዳል ነው ያሉት። ተቋማት በሚሰሩበት ሙያ ዕውቅና እንዲያገኙ የህግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት፣ የፍተሻ ስራና የቤተ-ሙከራ አገልግሎትን ማጠናከርና ተቋማትን መደገፍ ያስፈልጋል ብለዋል። ችግሮችን መፍታት የሚቻለው አምራቹና ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራሮችን ማጠናከር ሲችሉ መሆኑንም አስገንዝበዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም