የኢፌድሪ መከላከያ ጠቅላይ ኢታማጆር ሹም ጀነራል ሰዓረ መኮንን በተፈፀመባቸው ጥቃት ተሰውተዋል

53
ሰኔ 16/2011  የኢፌድሪ መከላከያ ጠቅላይ ኢታማጆር ሹም ጀነራል ሰዓረ መኮንንና ሜጀር ጀነራል ገዛኢ አበራ ትላንት በተፈፀመባቸው የተቀነባበረ ጥቃት ህይወታቸው ማለፉን የጠቅላይ ሚኒስትር ፕሬስ ሴክሬታሪያት አስታወቀ። የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ሴክሬታሪያት ኃላፊው አቶ ንጉሱ ጥላሁን በሰጡት መግለጫ ጀነራሎቹ የተገደሉት በተቀነባበረ መንገድ በጠባቂያቸው ነው። በአማራ ክልል ትናንት በተሞከረ የመፈንቅ ለመንግስት ርዕሰ መስተዳደሩ ዶክተር አምባቸው መኮንንና የአደረጃጀት ዘርፍ አማካሪያቸው አቶ እዘዝ ዋሴ ተሰውተዋል። በተጨማሪ የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ምግባሩ ከበደ በጥቃቱ በደረሰባቸው ጉዳት ህክምና እንዲከታተሉ እየተደረገ ይገኛል። ጥቃቱ የአማራ ክልልን ብቻ ሳይሆን የአገሪቱን ህዝብ በአጠቃላይ ወደብጥብጥ ለማስገባት ታስቦ የተፈጸመ መሆኑንም ነው አቶ ንጉሱ የገለፁት። ጥቃት አድራሾቹ አብዛሃኛዎቹ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረው ቀሪዎቹን በቁጥጥር ስር ለማዋል የፌደራል መንግስት ከክልሉ የፀጥታ ኃይል ጋር ተባብሮ እየሰራ መሆኑንም አመልክተዋል። የጀነራሎቹ የቀብር ስነ-ስረዓት ወታደራዊ ስርዓት በሚፈቅደው መልኩ ለማከናወን የሚያስችል ዝግጅት መደረጉንም ገልፀዋል። መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በጋራ በመቆም ወንጀለኞችን አሳልፎ በመስጠትና አካባቢያቸውን በመጠበቅ እንዲተባበሩ አቶ ንጉሱ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም