የሰሜን ሸዋ ዞን አርሶ አደሮች ምርታማነታቸውን ለማሳደግ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠየቁ

89
ደብረብርሃን ሰኔ 15/2011 በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን አርሶ አደሮች ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያደርጉት ጥረት በቴክኖሎጂ አቅርቦት መሣሪያዎች እንዲታገዝ ጠየቁ። አርሶ አደሮቹ  በደብረ ብርሃን ባለፉት ሁለት ቀናት ባካሄዱት የ2011/12 ምርት ዘመን  የሰብል ልማት የንቅናቄ መድረክ ላይ እንደተናገሩት የግብርና ሥራቸውን በዘመናዊ መንገድ በማካሄድ እያከናወኑ ያሉት እንቅስቃሴ ተገቢውን ድጋፍ እያገኘ አይደለም። በመሆኑም ምርታማነታቸውን በማሳደግ ኑሮአቸውን ለማሻሻልና ለአገር ኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽኦቸውን ለማሳደግ ዘመናዊ መሣሪያዎች ሊቀርቡልን ይገባል ብለዋል። በሞረትና ጅሩ ወረዳ የቦሎ ቀበሌ ሞዴል አርሶአደር ደጀኔ ዘለቀ  ከአካባቢያቸው አርሶ አደሮች ጋር በክላስተር ተደራጅተው 300ሄክታር መሬት ላይ  ጤፍ ምስር ለመዝራት በትራክተር በማሳረስ የጀመሩት ሥራ በቂ ሆኖ እንዳላገኙት ይናገራሉ። ትራክተሮቹ  በበቂ ሁኔታ ቢቀርቡ የአርሶ አደሩን ጉልበት ከብክነት ከማዳኑም በላይ በዓመት ለእርሻ፣ ለበሬ ኪራይና ለደቦ ድግስ የሚያወጡትን ከ20ሺህ ብር በላይ ወጪ መቀነስ ያስችለኝ ነበር በማለት ተናግረዋል። በኅብረት ሥራ ዩኒየኖች በኩል በመቅረብ ላይ ያሉት ትራክተሮች የአርሶ አደሩን ፍላጎት እያሟሉ ባለመሆናቸውን ተጨማሪ ትራክተሮች እንዲቀርቡላቸው ጠይቀዋል። በሲያደብርና ዋዩ ወረዳ የሮቢ ቀበሌ አርሶአደር ተሾመ ግርማ በበኩላቸው  በእርሻ ማሳ ጉርብትና ካላቸው አርሶ አደሮች ጋር በስንዴ ክላስተር ተደራጅተው በበሬ በማረስና ምርጥ ዘር ማዳበሪያ በመጠቀም  በሄክታር 67ኩንታል ማምረታቸውን ያስታውሳሉ። ሆኖም በትራክተር በማረስና ሰብል መሰብሰቢያና መውቂያ መሣሪያዎች መጠቀም ምርታማነታቸውን ከዚያም በላይ ለማሳደግ ብሎም የመሬት ለምነትን ለመጠበቅ አቅርቦቱ ሊሟላልን ይገባል በማለት ጥያቄያቸውን አቅርበዋል። ለዚህም ዩኒየኖች የጀመሩትን ውስን አቅርቦት እንዲያሻሽሉና መንግሥትም ቢሆን የእርሻ መሣሪያዎችን በነፍስ ወከፍ የሚገዙበትን ብድር ሊያመቻችልን ይገባል ብለዋል። የጥቁር አፈር ማጠንፈፊያ መሣሪያም እንዲቀርብላቸውም ጠይቀዋል። የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ መሰረት ኃይሌ አርሶ አደሮች ያነሷቸውን የቴክኖሎጂ አቅርቦት ችግሮች ለመፍታት ከአጋር ድርጅቶች ጋር እየተሰራ ነው ብለዋል። በዩኒየኖች በግል የቀረቡት 50 ትራክተሮች በምርት ዘመኑ በዞኑ ለማረስ ከታቀደው 57ሺህ ሄክታር መሬት እስካሁን ያረሱት 9 ሺህ ሄክታር መሬት ብቻ መሆኑን ተናግረዋል። የአርሶ አደሩን ቴክኖለጂ ፍላጎት ለማሟላት በቀጣይ ዓመት 50 የሰብል መውቂያ መሣሪያዎችና ስምንት የእርሻ ትራክተሮች ለመግዛት ከ20ሚሊየን ብር በላይ መመደቡን የገለጹት የወደራ የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ማህበር ዩኒየን የመካናይዘሽን ክፍል ኃላፊ አቶ መዝገቡ እሸቴ ናቸው። ሰሜን ሸዋ በአማራ ክልል በሰብል ምርታማነት ከሚታወቁ ዞኖች አንዱ መሆኑ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም