የኢትዮጵያ ስፖርት ሳይንስ ባለሙያዎች ማህበር ተመሰረተ

94
አዲስ አበባ ሰኔ 15/2011  የኢትዮጵያ ስፖርት ሳይንስ ባለሙያዎች ማህበር ዛሬ ተመሰረተ። ፕሬዚዳንት፣ ምክትል ፕሬዚዳንትና ሌሎች አባላቱንም መርጧል። ማህበሩ እንዲመሰረት የኩላቸውን ሚና የተወጡት የወቅቱ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠዋል። የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ አቶ ታምራት በቀለ ደግሞ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነዋል። እንዲሁም አቶ ሳሙኤል ስለሺ  በዋና ጸሀፊነት ፣ ወይዘሮ ጥሩወርቅ ብርሃኑ አቃቤ ነዋይ፣ አቶ ክፍሌ ሰይ እና አቶ ተሾመ አለማየሁ በኣባልነትና አቶ አባይ በላይሁን የህዝብ ግንኙነት ሆነው ተመርጠዋል። ዛሬ ከተመረጡት በተጨማሪ ሌሎች ሁለት ሴት ባለሙያዎች በቀጣይ በስራ አስፈጻሚነት እንደሚመረጡ ነው የተነገረው። የማህበሩ የበላይ ጠባቂ ደግሞ የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላየ ጌቴ ሆነዋል። የማህበሩ ምስረታ ዋና ዓላማ በዘርፉ ያሉ የባለሙያዎችን መብት ማስከበር ሲሆን ባለሙያዎቹ ያላቸውን እውቀትና ግንዛቤም ለአገር አስተዋጽኦ በማበርከት የበኩላቸውን እንዲወጡ ማድረግ ነው ተብሏል። በመላ አገሪቱ ከ10 ሺህ በላይ ከዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች የስፖርት ሳይንስ ትምህርት ወስደው የተመረቁና በተለያየ የሙያ ኃላፊነት ደረጃ ላይ እየሰሩ ያሉ ባለሙያዎች ይኖራሉ ተብሎ ይታሰባል። ማህበሩ እነዚህን ባለሙያዎች ባላቸው እውቀት ስፖርቱን እንዲያግዙና ራሳቸውም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ይሰራል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም