እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ በ26ኛ ሳምንት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች የቀን፣ የሰዓትና የቦታ ለውጥ አድርጓል

54
አዲስ አበባ ሰኔ 2/2010 የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የፊታችን ሰኞና ማክሰኞ በሚደረጉ የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች የ26ኛ ሳምንት መርሃ ግብሮች ላይ የቀን፣ የሰዓትና የቦታ ለውጥ ማድረጉን አስታወቀ። በዚሁ መሰረት ሰኞ ሰኔ 4 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ 11 ሰአት ከ30 ላይ ሊካሄድ የነበረው የመከላከያና ጅማ አባጅፋር ጨዋታ ማክሰኞ ሰኔ 5 ቀን 2010 ዓ.ም ከቀኑ 10 ሰአት ላይ ይካሄዳል። ማክሰኞ ሰኔ 5 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም ኢትዮጵያ ቡና ከአዳማ ከተማ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ 11 ሰዓት ከ30 ላይ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ከ30 ደቂቃ በኋላ 12 ሰዓት ላይ ይካሄዳል። ማክሰኞ ሰኔ 5 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም ኢትዮ ኤሌትሪክ ከቀኑ 9 ሰአት ላይ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ሰኞ ሰኔ 4 ቀን 2010 ዓ.ም ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ ይከናወናል። ሰኞ ሰኔ 4 ቀን 2010 ዓ.ም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወልዲያ ከተማ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ 9 ሰአት ላይ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ በዛው ቀን ከቀኑ 11 ሰአት ከ30 ላይ የሚካሄድ ይሆናል። በ26ኛው ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች መካከል በሰበታ ስታዲየም ሰኔ 4 ቀን 2010 ዓ.ም ከቀኑ 9 ሰአት እንዲካሄድ መርሃ ግብር የወጣለት የመቐለ ከተማና ፋሲል ከተማ ጨዋታ ከወቅቱ ዝናባማ የአየር ሁኔታ ጋር በተያያዘ በክለቦቹ ጥያቄ መሰረት በዕለቱ ከረፋዱ 4 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም እንዲካሄድ ተወስኗል። በክልል ከተሞች የሚካሄዱ የዚህ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች በወጣላቸው መርሃ ግብር መሰረት ከነገ በስቲያ ይካሄዳሉ። በይርጋለም ስታዲየም ሲዳማ ቡና ከድሬዳዋ ከተማ፣ በአርባ ምንጭ ስታዲየም አርባምንጭ ከተማ ከወላይታ ድቻና በአዲግራት ስታዲየም ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከደደቢት ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። በተያያዘ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ24ኛ ሳምንት መርሃ ግብር በይርጋለም ስታዲየም በሲዳማ ቡናና አዳማ ከተማ መካከል በተደረገው ጨዋታ ሲዳማ ቡና 1ለ0 አሸንፎ ነበር። በሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ብቸኛውን ግብ ያስቆጠረው አዲስ ግደይ አምስት ቢጫ እያለበት በጨዋታው ላይ ተሰልፏል። የፌዴሬሽኑ የስነ ምግባር ኮሚቴ ጉዳዩን በማጣራት ሲዳማ ቡና በጨዋታው ላይ አግባብነት የሌለውን ተጫዋች በማሰለፉ የሲዳማን የአሸናፊነት ውጤት በመቀልበስ አዳማ ከተማ በፎርፌ 3ለ0 አሸናፊ እንዲሆንና ሶስት ነጥብ እንዲያገኝ ወስኗል። በዚሁ መሰረት አዳማ ከተማ ነጥቡን ወደ 42 ከፍ በማድረግ እና ከጅማ አባ ጅፋር ጋር እኩል ነጥብ በመያዝ ብዙ ባገባ በሚለው ህግ የፕሪሚየር ሊጉ መሪ መሆን ችሏል። የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ አዳማ ከተማ፣ ጅማ አባጅፋር፣ መቐለ ከተማና ቅዱስ ጊዮርጊስ በተመሳሳይ 42 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው በቅደም ተከተል ከአንድ እስከ አራት ያለውን ደረጃ ይዘዋል። አርባ ምንጭ ከተማ፣ ኢትዮ-ኤሌትሪክና ወልዲያ ከተማ በቅደም ተከተል ከ14ኛ እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ በወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ። የሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት የጅማ አባጅፋሩ ናይጄሪያዊው ተጫዋች ኦኪኪ አፎላቢ በ16 ጎሎች ሲመራ፤ የደደቢቱ ጌታነህ ከበደ በ11 እንዲሁም የኢትዮ- ኤሌክትሪኩ ጋናዊ ተጫዋች አልሃሰን ካሉሻ በ10 ግቦች ይከተላሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም