መንግስት በካፒታል በጀት ላይ ጭማሪ ማድረጉ የስራ እድል ፈጠራን ያሳድጋል ተባለ

71
አዲስ አበባ ሰኔ 15/2011 በቀጣዩ በጀት ዓመት መንግስት በካፒታል በጀት ላይ ጭማሪ ማድረጉ የስራ እድል ፈጠራን የሚያሳድግ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያ ተናገሩ። የፌዴራሉ መንግስት ለ2012 በጀት ዓመት 387 ቢሊዮን ብር ረቂቅ በጀት መመደቡ ይታወቃል። በበጀት መግለጫው ላይ እንደተጠቀሰው ከተያዘው በጀት ውስጥ ለመደበኛ ወጪ 109 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር እና ለካፒታል 130 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ተመድቧል። ለክልሎች ድጋፍ የሚውል 140 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ሲሆን 6 ቢሊዮን ብር ደግሞ ለዘላቂ የልማት ግቦች የተመደበ ነው። የ2012 ዓ.ም ረቂቅ በጀቱ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጻር የ6 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ጭማሪ አሳይቷል። በረቂቅ በጀቱ ዙሪያ በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩንቨርስቲ የዴቨሎፕመንት ኢኮኖሚክስ የትምህርት ክፍል መምህር አቶ መዚድ ናስርን አነጋግሯል። የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ከማይክሮ ኢኮኖሚው አንጻር መንግስት ፖሊሲዎችናስትራቴጄዎችን የሚያስፈጽመው በሁለት ዓይነት መንገድ እንደሆነ ያስረዳሉ። ወጪና ገቢን በተመለከተ በፊስካል ፖሊሲና በሞኒተሪ ፖሊሲ የወለድ ምጣኔን በመጨመር እና በመቀነስ መንግስት በኢኮኖሚው ላይ ያለውን የገንዘብ ፍሰት መቆጣጠር ነው። ወጪ በመንግስት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ውስጥ ኢኮኖሚው እንዲያድግ ወሳኝና ጠቃሚ የሆነ መሳሪያ እንደሆነና በጀትም በኢኮኖሚው ውስጥ ወጪ የሚለውን ጽንሰ ሀሳብ የሚይዝ እንደሆነ ይናገራሉ። በ2011 ዓ.ም ከነበረው በጀት አንጻር የ2012 ዓ.ም ረቂቅ በጀት የተወሰነ ለውጥ እንደታየበትና በካፒታል በጀት ላይ ጭማሬ ተደርጓል። በ2011 ዓ.ም በጀት ላይ የካፒታል በጀት የተወሰነ መቀነስ ታይቶበት እንደነበረና የካፒታል በጀት የስራ እድሎችን ለመፍጠር የሚጠቀም በመሆኑ ካፒታል በጀት እየቀነሰ በመጣ ቁጥር በኢኮኖሚ ውስጥ የስራ እድል የመፍጠር አቅም እየተቀዛቀዘ እንደሚመጣ አመልክተዋል። በመሆኑም በ2012 ዓ.ም ረቂቅ በጀት የካፒታል በጀት ላይ ጭማሬ መደረጉ መንግስት ለስራ እድል ፈጠራ የሰጠውን ትኩረት የሚያሳይ መሆኑን ባለሙያው ያስረዳሉ። የካፒታል በጀቱ መጨመሩ ለመንገድ፣ ለውሃ፣ ለትምህርትና ሌሎች አገልግሎቶች መሰተ ልማት ሲዘረጋ ሰው በመቅጠር የስራ እድል ፈጠራ እንደሚያገኙና የስራ እድል መፈጠሩ ሰዎች ገቢ እንዲያገኙ ያደርጋል ባይ ናቸው። ሆኖም ሰዎች ገቢ አግኝተው ግብይት በሚፈጽሙበት ወቅት የዋጋ ንረት እንደሚኖርም ከግምት ውስጥ ማስገባት ይግባል ብለዋል። የመደበኛ በጀት ከባለፈው ዓመት አንጻር የ14 ነጥብ 9 በመቶ እድገት መጨመሩም የአስተዳደራዊ ወጪዎች በተለይም የመንግስት ግዢዎች በስፋት ለማከናወንና በግዢዎቹም የግሉን ዘርፍ እንቅስቃሴ ለማሳደግ እንደሚረዳ ነው የምጣኔ ሃብት ባለሙያው የገለጹት። የመደበኛ እና የካፒታል በጀት መጨመሩ አጠቃላይ በበጀቱ ላይ የሚታዩ አሀዛዊ መረጃዎች በ2009 ዓ.ም ተመዝግቦ የነበረውን እድገት ዳግም ለማሳካት ያስችላልም ብለዋል። በ2012 ዓ.ም ረቂቅ በጀት ከታቀደው ገቢና በቀረበው ረቂቅ በጀት መካከል 97 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር የበጀት ጉድለት ታይቷል። የበጀት ጉድለቱን በቀጥታ በጀት ድጋፍና በፕሮጀክት ከሚገኝ ብድር፣ ከአገር ውስጥ ከሚገኝ ብድር ለመሸፈን ታቅዷል። በተወሰነ መልኩም በጀቱ ላይ አሳሳቢ የሚሆነው የበጀት ጉድለት ነው ያሉት አቶ መዚድ በአሁኑ ሰአት ኢትዮጵያ ከምታገኘው ገቢ የምታወጣው ወጪ በመጨመሩ የበጀት ጉድለት በየዓመቱ እየጨመረ መምጣቱን አንስተዋል። መንግስት የበጀት ጉድለቱን ለመሙላት ያስቀመጣቸውን እቅዶች በአግባቡ መፈጸም እንደሚገባውና በዚህም ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት አለበት ነው ያሉት። በክልሎች መካከል ያለውን የእድገትና የልማት ልዩነት ታሳቢ ባደረገ መልኩ በጀቱ መደልደል እንዳለበትም ጠቁመዋል። ክልሎች ከድህነት ቅነሳ፣ መሰረት ልማት ማስፋፋት፣ አገልግሎትን ተደራሽ ከማድረግና ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል ላይ መሰረት ባደረገ መልኩ በጀታቸውን እንዲያውሉም መክረዋል። ለዘላቂ ልማት ግቡ ስድስት ቢሊዮን ብር መመደቡም በተለያዩ መስኮች ኢትዮጵያ ለማሳካት ያቀዳቻውን ግቦች ማስፈጸም ወሳኝ ሚና እንዳለውና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታን ለማሻሻል እንደሚረዳም ጠቅሰዋል። ግንቦት 30 ቀን 2011 ዓ.ም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አራተኛ የስራ ዘመን 43ኛ መደበኛ ስብስባ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ የ2012 ዓ.ም ረቂቅ በጀት ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከቀረበው ረቂቅ በጀት ውስጥ 63 በመቶው ቅድሚያ ትኩረት ለሚሰጣቸው ለትምህርት፣ ለመንገድ፣ ለግብርና፣ ለውሃ፣ ለጤናና ለከተማ ልማት ወጪዎች መሆኑንም በዚሁ ጊዜ አንስተዋል። ''በበጀት ዓመቱ ከአገር ውስጥ የገቢ ምንጮችና ከውጪ አገር ዕርዳታ 289 ነጥብ 8 ቢሊዮን ለመሰብሰብ ታሳቢ ተደርጓል'' ብለዋል። በጀት የተበጀተላቸው መስሪያ ቤቶች በጀቱን ለታለመለት ዓላማ በቁጠባና በላቀ ውጤት ጥቅም ላይ ማዋል እንዳለባቸው ጠቁመዋል። ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ በጀት ላይ ሰፊ ውይይት ካደረገ በኋላ ለዝርዝር እይታ ለገቢዎች፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መምራቱ የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም