አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን በአፍሪካ ህብረት ሽልማት ሊበረከትለት ነው

190
አዲስ አበባ ሰኔ 15/2011 አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን ለወጣት አፍሪካዊያን አርአያ በመሆን ላበረከተው አሰተዋኦ በአፍሪካ ህብረት የዋሽንግተን ዲሲ ፅህፈት ቤት የእውቅና ሽልማት ሊበረከትለት ነው። በህብረቱ የዋሽንግተን ዲሲ ፅህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ፤ ቴዎድሮስ ካሳሁን ከኢትዮጵያም አልፎ ለመላ አፍሪካ ወጣቶች በአርዓያነት የሚጠቀስ አርቲስት መሆኑን አመላክቷል። በመጪው ሃምሌ ወር በዋሽንግተን ዲሲ በሚካሄደው የአፍሪካ ሩጫ ጋር ተያይዞ በሚሰናዳው ዝግጅት ላይ ሽልማቱ እንደሚበረከትለት ታውቋል። በዋሽንግተን የአፍሪካ ህብረት ፅህፈት ቤት ዋና ተጠሪ ዶክተር አሪካና ችሆምቦሪኮ ሽልማቱን አስመልክተው በሰጡት አስተያየት አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን ከኢትዮጵያም አልፎ ለመላ አፍሪካ ወጣቶች አርዓያ ነው። አርቲስት ቴድሮስ ካሳሁን በሙዚቃው ዘርፍ ተግቶ በመስራት ለአፍሪካ ወጣቶች ያበረከተዉ አስተዋፆ የጎላ በመሆኑ የሚሰጠው እዉቅና ትርጉም ያለው መሆኑንም ተናግረዋል። ከመድረክ ሥራዎቹ ባሻገር የበጎ አድራጎት ክንውኖቹ የአፍሪካ ህብረት ዝግጅቶቹን ተጠቅሞ ለማጉላትና የራሱን አሻራ ለማሳረፍ ከተነሳባቸዉ ዓላማዎች መካከል መሆናቸውንም ዶክተር አሪካና ችሆምቦሪኮ ጠቁመዋል። የታላቁ የአፍሪካ ሩጫ ውድድር ዋና አዘጋጅ የሆኑት ዶክተር ጋሻው አበዛ በበኩላቸው ፤ ለአርቲስቱ የሚበረከተው ሽልማት ወቅታዊ፣ ምክንያታዊና ለኢትዮጵያዊያንም አኩሪ መሆኑን ገልፀዋል። ለአርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን የሚሰጠው እውቅና ካበረከተው ተምሳሌታዊ ሚና ባሻገር ለአፍሪካ አህጉርም ኩራት መሆኑን ተናግረዋል። የሩጫ ውድድሩ የተዘጋጀው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባለፈው ዓመት በሰሜን አሜሪካ ሶስት ከተሞች በነበራቸው ጉብኝት በዋሽንግተን ዲሲ ከሚገኙ ኢትዮጵያን ጋር በነበራቸው ውይይት ቀኑ የኢትዮጵያ ቀን ሆኖ እንዲከበር የከተማው ከንቲባ መወሰናቸውን ተከትሎ ነው። በመጪው ሃምሌ 14 ቀን 2011 ዓ.ም "ታላቁ የአፍሪካ ሩጫ" በሚል የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በዋሽንግተን ዲሲ ይካሄዳል። ውድድሩ በዋሽንግተንዲሲ የአፍሪካ ህብረት ፅህፈት ቤትና የኢትዮጵያ ኢምባሲ፣ ኖቫ ኮኔክሽንስ በሚባል የበጎ አድራጎት ድርጅትና በዋሽንግተን ዲሲ የከንቲባ ፅህፈት ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ክፍል ጋር በመተባበር የተዘጋጀ መሆኑም ተገልጿል። የሩጫ ውድድሩ በሺህዎች የሚቆጠሩ ተሳታፊዎች ከተጋባዥ ታዋቂ የአፍሪካ አትሌቶች ጋር የሚሳተፉበት መሆኑንም ከአዘጋጆቹ የተገኘው መረጃ ያመላክታል። ታላቅ የአፍሪካ ሩጫ በዲሲ በየአመቱ የሚካሄድ ብዙሃኑን የሚያሳትፍ የጎዳና ላይ ሩጫ መሆኑ ይታወቃል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም