ድህነትን በጥረቱ ያሸነፈው አፍሪካዊ

282

በታዬ ለማ (ኢዜአ)

የቢቢሲ ጋዜጠኛ ጉዞውን ወደ አንድ ትንሽ የገጠር መንደር አድርጓል፡፡ መሰረተ ልማት  ያልተሞላላት ድህነት የነገሰባት ይች የገጠር መንደር   በምዕራባዊቷ አፍሪካ አገር ሴኒጋል  ትገኛለች፡፡  በአፍሪካ ድህነት ጎልቶ ከሚታይባቸው የገጠር መንደር  አንዷ ስትሆን  በድህነት የሚኖሩ በርካታ ጎስቋላ  ነዋሪዎች ያሉባት ናት ።

ጋዜጠኛው  ወደ መንደሩ  የሚያደርገውን ጉዞ   በአቧራ የተሞላ መንገድ ፍጹም  ያልተመቸ በመሆኑ  ጉዞውን አድካሚ አድርጎበታል ። የጋዜጠኛው ጉዞ  ስሙ ስለገነነው በዚች ትንሽ መንደር ስለተገኘው ዝነኛ  ኳስ ተጨዋች ሰይዶ ማኔ ማወቅ ስለነበር  ምቹ ያልሆነው አድካሚው ጉዞ ያሰበበት መንደር  ከመድረስ አላገደውም ፡፡

ጋዜጠኛው በድህነት ከተጎሳቁለው መንደር የሰይዶ ማኔ ትውልድ መንደር ባምቤሌ ሲደርስ ሰይዶ ማኔን ቤተሰብ ለማግኘት እንደሚፈልግ የአካባቢውን ነዋሪዎች ይጠይቃል፡፡   ከዚህ ከደሀ መንደር ወጥቶ ስምና ዝናው በአለም ስለናኘው ሰይዶ ማኔ ማንም የማያውቅ የለምና ያሰበውን ለማግኘት ምንም ያህል ግዜ አልፈጀበትም፡፡

ዛሬ በሊቨርፑል ክለብ ስኬታማ የሆነው የሰይዶ ማኔ ቤተሰቦች ቤት ሲደርስም  በቤቱ  ውስጥ በርካታ ሰዎችን ያገኛል።

የነማኔ ወላጅ ቤት የሊቨርፑልና  የማንችስተር ሲቲን የመጨረሻ ወሳኝ ጨዋታ በሚመለከቱ የአካባቢው ሰዎች ከአፍ እስከ ገደብ ተሞልቷል፡፡

ጋዜጠኛው በነማኔ ቤት የሚፈልጋቸው ሁለት ሰዎች ግን  ይህን ዓለም የሚጠብቀውን በተለይ የባምቤሌ ነዋሪዎች  በጉጉት የጠበቁትን ጨዋታ ለማየት ፈጽሞ አልፈለጉምና ከቦታው የሉም፡፡

ሁለቱ ሰዎች የሰይዶ ማኔ ወላጆች ናቸው፡፡ ወላጆቹ የልጃቸውን መውደቅ መነሳት ስለሚያስጨናቃቸውና የወላጅ አንጀታቸው ስለማይችል ሁሌም ቢሆን ጨዋታውን እንደማይመለከቱ ጋዜጠኛው ከአካባቢው ነዋሪዎች ይረዳል፡፡

ከቤቱ በመውጣትም  ወደ ሰይዶ አባት አል አጂ ታሊቦ ስለ ሰይዶ  ማኔ መረጃ ለማግኘት ወደ ሚገኙበት መስጊድ ጉዞውን አደረገ፡፡ አባቱንም  በመስጊድ ሲሰግዱ አግኝቷቸው መጨዋወት  ጀምሩ

“ልጆት ምን አይነት ሰው ነው” ሲል ይጠይቃቸዋል። አባትም “ልጄማ  ከእግር ኳስ ተጫዋች በላይ ነው“ ሲሉ ፈገግታ በተሞላበት ለልጃቸው ያላቸውን አድናቆት ለጋዜጠኛው ይነግሩታል፡፡ “ሰይዶ በጣም ታታሪ ልጅ ነው፡፡ ሁሉንም ሰዎች ማስደሰት የሚፈልግ፡፡  ሃይማኖቱን የሚያከብር “ ሲሉም ስለ ልጃቸው ታታሪነት ያስረዱታል፡፡

የሰይዶ ማኔ አባት ስለ ልጃቸው ይህን ብለው ሊያቆሙ አልፈለጉም፡፡ ” ምን ይህ ብቻ ሰይዶ እኮ የተለየ ነው፡፡ ልጅ ህጻን አዋቂ ሳይል የሚያከብር፡፡ ድህነቱን ማንነቱን የማይረሳ፤ ሰፈሩን አካባቢውን የሚወድ”  ሲሉም ያሞካሹታል ፡፡

” ከእንግሊዝ  ወደ አካባቢው ሲመጣ  እንደ ታዋቂ መምሰል አይፈልግም፡፡ አካባቢውን መስሎ ነው የሚመጣው፤  ልጄ  ትሁትና ሰው አክባሪ መሆኑን በዚህም ባህሪው ሁሉም የባምቤሊ ሰው የሚወደው “  ሲሉ ነው ስለ ልጃቸው  ጋዜጠኛውን ያጫወቱት።

በእርግጥ ሰይዶ ማኔ በአካባቢው ተወዳጅ ሰው ነው፡፡ እሱ ለከተማዋ ለነዋሪዎች ትልቅ ትምህርት ቤት በማስገንባቱ  ሳይሆን በባህሪው በትህትናው  የከተማው ነዋሪዎች የተለየ ፍቅር ይሰጡታል ሲሉ አጎቱ ኢብራሂም ቱሬ ይናገራሉ፡፡

ለዚህም ይመስላል ሰይዶ ማኔ ወደ ከተማዋ  በመጣ ቁጥር  እያንዳንዱ ሰው እንኳን ደህና መጣህ ሲሉ በፍቅርና በደስታ በነቂስ ወጥተው የሚቀበሉት ይላሉ አጎቱ።

የሰይዶ ማኔ ከምንም ተነስቶ ለዚህ ስኬት መድረስ ብዙ የአካባቢው  ህጻናት ነገ ድህነትን በማሸነፍ  ታዋቂና ዝነኛ መሆን እንደሚችሉ ትምህርት ሰጥቷል ያለው ደግሞ በአካባቢው የሚገኙ ህጻናትን የሚያሰለጥነው ዳያናባ ዳያታ ነው።

በዚች መንደር  ህጻናት “እኔ ሰይዶ  ማኔ ነኝ” ሲሉ በጎዳናዎች ኳስን ከዚህ ወደ እዚያ ስያሽከረክሯት ይውላሉ ሲል ነገ በርካታ ሰይዶ ማኔዎች በአካባቢው ሊፈሩ እንደሚችሉና  ህፃናቱ ለእግር ኳስ ያላቸው ፍቅር እንዳደገ እንደመጣም ለቢቢሲ ተናግሯል።

ዛሬም ድረስ መንገድ በሌላት፣  ትምህርት ቤት ብርቅ በሆነባትና ውሀ  እንኳን ከማይገኝባት  በትንሿ የገጠር መንደር ተወልዶ  የሻምፒዮንስ ሊግ ክብርን ከሊቨርፑል ጋር ያሳካው ሰይዶ ማኔ፤  እዚህ ደረጃ ለመድረስ ታዲያ ብዙ ውጣ ውረድ ማሳለፉን ተዋቂዋ የስፖርት ጋዜጠኛ   ሜሊሲያ ሬዲ  ትናገራለች፡፡

እግር ኳስ ተጨዋች ብቻ መሆን ነው የምችለው ብሎ  መልፋቱና በእግር ኳስ ተስፋ የሚያስቆርጡ በርካታ ጉዳዮችን ማሸነፍ መቻሉ ለዚህ እንዳበቃው  የገጠመውን ውጣ ውረዶች እንዳጫወታት ደቡብ አፍሪካዋ እውቋ የስፖርት ጋዜጠኛዋ ሜሊሲያ ተናገራለች።

የሰይዶ ማኔ እንቅፋት የጀመረው ያኔ ህጻን እያለ ኳስ ምን እንደሆነች እንኳን ሳያውቅ ግን ማንከባለል በሚወድበት ወቅት ነው ትላለለች ሜሊሲያ ፡፡

ያኔ አባቱ አንተ ልጅ ይህን ኳስ ተው ሲሉ ይመክሩት ይገጽሱት እንደ ነበር ትተርካለች ፡፡

የከተማው ምርጡ ተጫዋች ተብሎ በአካባቢው ቢሞካሽም፤ ወደ ፊት ተጫዋች ሊሆን እንደሚችል በጓደኞቹና በአካባቢው ኳስ አፍቃሪዎች ቢነገረውም፤ አባቱ ግን ኳስ እንዳይጫወት የሚያደርጉት ጫና እረፍት የሚነሳ እንደነበር ማኔ ለማሊሲያ ተርኮላታል፡፡

የሰይዶ ቤተሰቦች ልጃቸው ሃይማኖተኛ ሆኖ፤ ሳይማር ያስተማረውን ቤተሰብ እንዲለውጥ እንጂ በሚወዳት ኳስ  እሱንና ቤተሰቡን ይቀይራል የሚለው  እንኳን በውናቸው  በህልማቸውም አስበውት አያውቁም ነበር፡፡

” ቤተሰቤ ሃይማኖቴን እንዳጠብቅና እና በሌላ ዘርፍ እንድሰማራ ነው የሚፈልገው፡፡ የኔ ልብና ጭንቅላት ደግሞ እግር ኳስና እግር ኳስ  ብቻ ነው፡፡   ከእግር ኳስ ውጭ ምንም ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡” የሚለው ሰይዶ እግር ኳስ ተጫዋች ለመሆን አባቱን ማሳመን ከባድ እንደ ነበር ያስታውሳል፡፡

ግን ከብዙ ጥረትና ሽምግልና በኋላ  ቤተሰቦቹ ኳስን እንዲያንከባልል እንደፈቀዱለት ያስታውሳል ፤ ከዚያ በኋላ ነው እንግዲህ የአስራ አምስት አመት ታዳጊ እያለ ከአጎቱ ጥቂት ገንዘብ  ወስዶ  ብዙ ኬሎሜትሮችን በማቋረጥ እግር ኳስ ተጫዋች ለመሆን ፈተና ለመፈተን  ወደ ዋና ከተማዋ ዳካር የተጓዘው ፡፡

ዳካር ሰይዶ ማኔን አጇን ዘርግታ አላቀፈችውም።  ሌላ እንቅፋት ጨመረችለት እንጂ፡፡ በዳካር  ወዶ ያላመጣው ድህነት እግር ኳስ ተጫዋች እንዳይሆን እክል እንደፈጠረበት ነው ጋዜጠኛዋ  የገለጸችው።

ሰይዶ ወቅቱን ሲያስታውስ  “በዳካር በርካታ ልጆች እንደኔው ተጫዋች ለመሆን  ለመፈተን በቦታው ተገኝተዋል፡፡ እነሱ በጣም የተደራጁ ናቸው፡፡ አዲስ ታኬታ ማሊያና ቁምጣ ያደረጉ የቡድን ተጫዋች ነው የሚመስሉት፤ እኔ ደግሞ በተቃራኒው ጫማም ሆነ ማልያዬ የተቀዳደና አሮጌ ነበር፡፡“ ይላል።

ገጠመኙን መቼም እንደማይረሳ የሚገልጸው ሰይዶ፤ ታዲያ በወቅቱ አንድ ሜዳው ላይ የነበረ አንድ ሽማግሌ ሰው ወደ እሱ መጥቶ  ማሊያውን ታኬታውን እያየ የተሳሳተ ቦታ እንደመጣ እንደነገረውና ቦታውን እንዲለቅ እንደጠየቀው አይረሳውም።

ሽማግልው ወደ እሱ ተጠግቶ “እግር ኳስ  ልትሞክር ነው“ የመጣው ብሎ ለጠየቀው ጥያቄ “አዎ”  ሲል ትንሹ ሰይዶ ማኔ መልስ ሰጠ፡፡  ሽማግሌው የተቀዳደደ ጫማ ና ማሊያ ያደረገውን ሰይዶ ማኔን በደንብ ተመለከተ፡፡ ከእግር እስከ እራሱ ገለማመጠው፡፡ “በዚህ ባደረከው አሮጌና የተቀዳደ ጫማ ነው የምትጫወተው?” ሲል ጫማዎቹንም በደንብ እያያቸው  “እንዴት በዚህ ትጫወታለህ “ ሲል ደግሞ ጠየቀው፡፡

“በእርግጥ ለሙከራ ያደረኳቸው ጫማዎች አሮጌና የተቀዳደዱ ናቸው፡፡ግን ምንም አማራጭ የለኝም በወቅቱ ከዚህ በላይ አቅም የለኝም  ” የሚለው ሰይዶ ማኔ ሰውየው ግን በዚህ እንዳላበቃ ይናገራል። “በዚህ ቁምጣ ነው የምትጫወተው? ይህ ያደረከው ቁምጣ ለኳስ የሚሆን አይደለም” ሲል አሁንም ታዳጊውን ተስፋ ሊያስቆርጠው ሞከረ፡፡

ሰይዶ ግን ተስፋ አልቆረጠም። “ይህ ያለኝ ምርጡ ቁምጣ ና ማሊያ ነው፡፡  ከዚህ በለይ ማምጣት አልችልም ” ሲል እንደነገረው  ወቅቱን ያስታውሳል።

ሽማግሌው አሰልጣኝ ጫማውንና ቁምጣውን ረስቶ ለሙከራ እድሉን እንዲሰጠውና ተፈትኖ  እራሱን ለማሳየት ኪሎ ሜትሮችን አቆርጦ የመጣው ሰይዶ አሰልጣኙን ለመነው፡፡   አሰልጣኙም ለታዳጊው ተስፋ በመቁረጥ ስሜት እድሉን ሰጠው፡፡

ሽማግሌው አሰልጣኝ በሰይዶ  የሜዳ ላይ ችሎታ ተደነቀ፡፡ ማሊያና ጫማ ብቻውን እግር ኳስ እንደማይጫወትም ያኔ በደንብ ተረዳ፡፡ ጥቁሩን ታዳጊ ጠራውና ፈተናውን ማለፉንና ከዛ ቀን በኋላም  ለሱ ቡድን እንደሚጫወት ነገረው ፡፡

ከ500 ማይል በላይ ርቀትን አቆርጦ በተቀደደ ጫማ ተጫውቶ ስኬታማ መሆን ቻለው ሰይዶ፤  የእግር ኳስ ህይወቱም አንድ ብሎ ጀመረ፡፡  ከዚያ በኋላ ከእናት ከአባቱ ተለይቶ ኑሮውን ዳካር አደረገ።

ታዳጊው  ወደ ትልቅ ስኬት ለመሸጋገር የመጀመሪያውን ፈተና ለማለፍ እናቱን አባቱን ጥሎ በዳካር በሚገኝ አንድ አካዳሚን ተቀላቀለ። ሙከራውን ካለፈ በኋላም በዳካር ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ አልሆነለትም፡፡ ዳካር ዘምድ አዝማድ የሌለው በመሆኑ የማረፊያ ቦታ ሌላ መከራ ሆነበት፡፡ በመጨረሻም በሰው በሰው ከማያወቃቸው ቤተሰቦች ጋር በመገናኘት   ከማያውቃቸው ቤተሰቦች ጋር ለስኬቱ ጉዞ ሲል  ለመኖር ተገደደ።

እንደ እድል ሆነና ሰዎች ለሰይዶ መልካም ቤተሰብ ሆኑለት፡፡  ያሰበው እስኪሳካለት ድረስም ተንከባከቡት። ለእግር ኳስ ጨዋታ የሚያስፈልገውን ትጥቅ ና ሌሎች ነገሮች እንዳሟሉለት  የሚያስታውሰው ሰይዶ፤ ዛሬም ለነዚህ በጎ ቤተሰብ ምስጋና ከማቅረብ አልተቆጠበም።

ሰይዶ  በዳካር የሚገርም  ችሎታውን ማሳየቱን በመቀጠሉ “ይህ ታዳጊ እንዳያመልጠኝ” ሲል የፈረንሳዩ ሜትዝ ክለብ ወደ ፈረንሳይ ይዞት ኮበለለ፡፡ ሰይዶ ማኔ ከትንሿ መንደር ወደ ዳካር ካዛም ወደ ፈረንሳይ ጉዞ አደረገ፡፡ የስኬት ጉዞውም ተጀመረ፡፡

ከፈረንሳይ የጀመረው የዚህ የጥቁር አፍሪካዊ ስኬት ወደ ኦስትሪያ ከዛም ወደ አገር እንግሊዝ ተሸጋገረ፡፡ ከሜትዝ ወደ ሬድ ቡል ሳልዝበርግ፤  ከዛም  ወደ ሳውዝአምፕተን ክለብ ጥቁሩ አፍሪካዊ ጉዞውን አደረገ ፡፡ በሳውዝአምፕተንም  ታላቅነቱን አስመሰከረ፡፡

በሳውዝአምፕተን ያሳየው ስኬት ታዲያ የእንግሊዙ ታላቅ ክለብ የሆነው ማንችስተር ዩናይትድ ይህን አፍሪካዊ ማንም ሳይቀድመኝ ሲል የሳውዝ አምፕተንን ደጃፍ መመላለስ ጀመረ፡፡

ሳውዝ አምፕተን ተጨዋቹን መሸጥ እንደማይፈልግ  ከአንዴም ሶስቴ ለማንችስተር መለሰ ሰጠ

በኋላ ግን ሌላው የአንግሊዝ ክለብ ሊቨርፑል ተጨዋቹን ለመውሰድ የሳውዝአምፕተንን በር ደጋግሞ አንኳኳ፡፡ በሩም ተከፈተለት፡፡ አፍሪካዊውን አልማዝ የአንፊልዱ ክለብ በ34 ሚሊዮን ፓውንድ የራሱ አደረገ ፡፡

በሊቨርፑልም ሰይዶ ተወዳጅና ዝነኛ ተጫዋች ሆነ። ከክለቡ ጋርም ብዙ ተጨዋቾች  የሚመኙት ጥቂቶች ግን የሚያሳኩትን የአውሮፓ ሻምፒዮን ሊግ በማሸነፍ ታሪክ ሰራ፡፡ የባምቤሊን ነዋሪዎች እንዲፈነጥዙ አደረገ፡፡

ባምቤሊ  አሁንም ቢሆን ብዙ የመሰረተ ልማት ችግር ያለባት መንደር  ናት፡፡ መንግስት ለነዋሪው መንገድ አሰራለሁ ብሎ ቃል ቢገባም እስካሁን ድረስ መንገድ አልገነባላትም፡፡ ነዋሪዎቹ ከዚህ በኋላ  መንግስት መንገዱን ይሰራልና ብለው ተስፋ ማድረግ ትተዋል ፡፡

አሁን እነሱ ተስፋ ያረጉት ከምንም ተነስቶ ከመንደራቸው ወጥቶ በአብት ላይ አብት፣ በስኬት ላይ ስኬት እየደራረበ ደረጃውን የጠበቀ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያሰራላቸው ልጃቸውን ሰይዱ  ማኔ መንገዱን እንደሚሰራላቸው ሙሉ እምነታቸውን ጥለዋል ፡፡

የተወለደበትን ደሀዋን መንደር ያልረሳው ሰይዶም  የወገኖቹ ችግር ችግሩ በመሆኑ ምላሽ ለመስጠት ብቻ ሳይሆን ነገም  ትላልቅ ስኬት በማስመዝገብ ለከተማዋ ብቻ ሳይሆን ለአገሩ ኩራት ለመሆን ጠንክሮ እንደሚሰራ ይናገራል፡፡

የአፍሪካ ዋንጫም አገሩን የዋንጫ አሸናፊ በማድረግ ባምቤሊ  ነዋሪዎችን ብቻ ሳይሆን መላው ሴኒጋላውያንን ለማስደሰት ቡድኑን በአንበልነት እየመራ ግብጽ ደርሶል፡፤

“ዛሬ እዚህ ደረጃ መድረሴ ይገርማል፡፡ ብዙ ነገሮች ተስፋ አስቆራጭ ነበሩ፡፡ ይህ ግን ህይወት ነው፡፡  ይህንን በጥንካሬ አልፌዋለሁ፡፡ ምንም ነገር በቀላሉ ማግኘት አይቻልም” ሲል ለጎል ድህረ ገጽ የተናገረው  ሰይዶ  በምንም ነገር ተስፋ መቁረጥ እንደማይገባ ተናግሯል፡፡

አለማችን ከሚገኙ ምርጥ ጥቂት ተጨዋቾች ሰይዶ ማኔ  አንዱ  ለመሆን ችሏል፡፡  በአሁኑ ወቅት በርካታ አውሮፓ ታላላቅ  ክለቦች ሰይዶ እንዲጫወትላቸው ቢፈልጉም የሊቨርፑል ደጋፊዎች ደግሞ ረጅም አመት የናፈቁትን የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ከኋደኞቹ ጋር ሆኖ በሚቀጥለው የውድድር አመት እንዲያመጣላቸው ይፈልጋሉ፡፡

ከምንም ተነስቶ አብት በአብት ዝና በዝና መሆን ይቻላል ፡፡  ተስፋ ባለመቁረጥ ያለሙት እስኪሳካ ጥረት ከተደረገ  መለወጥም  ስኬታማ መሆን እንደሚቻል  በዛች የገጠር ከተማ ተወልዶ የረባ ምግብ እንኳን ሳይበለላ በባዶ እግሩ ኳስ በመጫወት እዚህ የደረሰው አፍሪካዊ ምሳሌ ነው። ቸር እንሰንብት፣