‘’ የሰማእታትን በዓል ስናከብር የወደቁለትን አላማ ከዳር ለማድረስ ቃላችን በማደስ ሊሆን ይገባል’’ ም/ር/ መስተዳድር ደብረ ጽዮን

80
መቐለ ሰኔ 15 / 2011 ''የሰማእታትን ቀን ስናከብር የወደቁለትን አላማ ከዳር ለማድረስ ቃላችን በማደስ ሊሆን ይገባል''ሲሉ የትግራይ ክልል ምክልትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል አስገነዘቡ። የሰማእታት ቀን ለ31ኛ ጊዜ መቐለ በሚገኘው የሰማእታት ሃውልት ዛሬ ተከብሯል። በበዓሉ ከፍተኛ የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ(ህወሓት) አመራሮችና የከተማው ነዋሪዎች የተገኙ ሲሆን፣ አመራሮች፣ የሰማእታት ቤተሰቦች፣ ነባር ታጋዮችና አካል ጉዳተኞች ጨምሮ የተለያዩ አካላት በሃውልቱ ስር የጉንጉን አበባ አስቀምጠዋል። ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት እንዳሳሰቡት ለህዝባዊ አላማ ተሰልፈው ክቡር ህይወታቸው የሰጡት ሰማእታት ስናስታውስ አደራቸውን በመጠበቅና የወደቁለትን አላማ ከዳር በማድረስ ሊሆን ይገባዋል። የሰማእታትን ቀን የምናከብረው የትግራይ ልጆች ብቻ ሳይሆን፤ ለህዝባዊ ዓላማ ተሰልፈው ክቡር ህይወታቸው የከፈሉትን ሁሉም ኢትዮጵያውያን ነው ብለዋል። ሰማእታትን ሁሌ የምናስታውሳቸው ቢሆንም ፤ የዛሬ 31 ዓመት ለገበያ በወጡ ንፁሃን ዜጎች አሰቃቂ ጭፍጨፋ የተፈፀመበት በመሆኑ ሁሌም አንረሳውም ሊሉ ዶክተር ደብረጽዮን ተናግረዋል። በበዓሉ ላይ ከተገኙት የመቐለ ከተማ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ቦሶና ያሬድ እንደገለጡት እነሱ በከፈሉት መስዋእትነት በአገራችን ሰላም ሰፍኖ የልማት ስራዎች ተጠናክረው ማየታቸው እንዳስደሰታቸው ገልጠዋል። መስዋእትነቱ አሁን ላለው እድገት የተከፈለ ዋጋ መሆኑን ማወቅና መረዳት ያስፈልጋል ያሉት ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ሰይፉ አዲሱ፣ ወጣቱ ትውልድ ሰላሙን በማስጠበቅ ሊተጋ ይገባዋል ብለዋል። በዛሬው ዕለት የሚታሰበው የሰማዕታት ቀን የደርግ መንግሥት ሰኔ 15 ቀን 1980 በሐውዜን ከተማ ገበያ ከ2ሺህ 500 በላይ ሰላማዊ ዜጎችን በጦር ሄሊኮፕተሮች ድብደባ የጨፈጨፈበት ቀን በመሆኑ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም