በቀጣዮች አስር ቀናት ዝናብ ሰጪ የሜቲዮሮሎጂ ገፅታዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ

62
ሰኔ 14/2011 በቀጣዮቹ አስር ቀናት ዝናብ ሰጪ የሜቲዮሮሎጂ ገፅታዎች ይበልጥ ተጠናክረው  እንደሚቀጥሉ  ብሄራዊ  ሜቲዮሮሎጂ  ኤጀንሲ  አስታወቀ። እየጣለ ያለው ዝናብ ሁሉም የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ ቦታዎችን የሚያዳርስ እንደሚሆንም ነው ኤጀንሲው የተነበየው። ኤጀንሲው ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው በቀጣዮች አስር ቀናት ዝናብ ሰጪ የከባቢ አየር ክስተቶች እየተጠናከሩ ሊሄዱ ይችላሉ። ከዚህ ጋር ተያይዞ  በተለይም ምዕራባዊ የሀገሪቷ ክፍል አጋማሽ ላይ የተጠናከሩ የደማና ክምችቶች ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ሊኖር እንደሚችልም ትንበያው ያስረዳል ተብሏል። ይህ ሁኔታ በክረምት ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች ላይ ለግብርና እንቅስቃሴ በጎ ጎን እንደሚኖረውም ይጠበቃል። በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ የሚጠበቀው ከባድ ዝናብ በተለይም ባለፉት ቀናት ተከታታይ ዝናብ እያገኙ ባሉ ቦታዎች ላይ የአፈር ውስጥ እርጥበትን ሊያበዛ እንደሚችልም ይጠበቃል። በተጨማሪም ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የአፈር መሸርሸርና ከመሬት መንሸራተት ጋር የተያየዙ ችግሮችን ሊያስከትል ስለሚችል አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም ኤጀንሲው አሳስቧል። አልፎ አልፎ በጥቂት ቦታዎች ላይ ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ ሊኖር ስለሚችል ከዚህ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ቦታዎችና ለጎርፍ ተጋላጭ አካባቢዎች ላይ ትኩረትና ክትትል ያስፈልጋልም ብሏል ኤጀንሲው። የሚከሰተው ከባድ ዝናብ ቅፅበታዊ ጎርፍ ሊያስከትል ስለሚችልም ቅድመ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባም ኤጀንሲው አሳስቧል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም