ዩኒቨርሲቲው የተሻሻሉ የእንሰት ዝርያዎች ለማግኘት ምርምር ላይ ነው

122
አዲስ አበባ ሰኔ 2/2010 የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በደቡብ ክልል በስፋት ለምግብነት በሚውለው የእንሰት ተክል ላይ ምርምር እያደረገ መሆኑን አስታወቀ። የዩኒቨርሲቲው የምርምርና የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ሲሳይ ሸዋአማረ በተለይም ለኢዜአ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው በተክሉ ላይ ምርምር ማድረግ የጀመረው ከሶስት ዓመታት በፊት ነው። ምርምሩ ለእንሰት ምርታማነት፣ ማህበረሰቡ የተሻለ የአመጋገብ ስርዓት እንዲኖረውና ለምግብነት የተሻሻሉና በሽታ የመከላከል አቅም ያላቸውን የእንሰት ዝርያዎችን በምርምር ለይቶ ለማባዛት ያለመ መሆኑን ነው የተናገሩት። በዚህም ከ120 የሚሆኑ የእንሰት ዝርያዎችን በመምረጥ በሽታ የመከላከል አቅም ያላቸውን በመለየት የማባዛት ስራ ጀምረናል ብለዋል። 'እንሰት በቀላሉ በባክቴሪያ የሚጠቃ ተክል ነው' ያሉት ዶክተር ሲሳይ፤ ማህብረሰቡ ጤናማ የእንሰት አመጋገብ ስርዓት እንዲኖረው በዩኒቨርሲቲውና በማህበረሰቡ ማሳ ባለሙያዎችን በመላክ ከበሽታ እንዴት መከላከል እንደሚቻል ትምህርትና ስልጠና እንደሚሰጥ ተናግረዋል። ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ በተለያዩ ቦታዎች የእንሰት ዝርያዎችን በባክቴሪያ በማጋለጥና በመለየት በሽታ የሚቋቋሙ ዝርያዎችን አባዝቶ ለማህበረሰቡ ለማከፋፈል በምርምር ላይ መሆኑን ነው ያስረዱት። በሌላ በኩል የእንሰት ተክል በመፋቅ ለምግብነት ማዋል በተለይም ለእናቶች አድካሚ መሆኑን ጠቅሰው፤ ዩኒቨርሲቲው ጉልበት የማይፈልግና በቀላሉ ወደምግብነት ለመቀየር የሚያስችል ቴክኖሎጂ በባለሙያዎች መስራቱን ገልጸዋል። ቴክኖሎጂው መስተካከል ያለበት ዲዛይን እንዳለውና በ2011 ዓመት ከቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር አስተካክሎ በማባዛት ማህበረሰቡን እያደራጀ ለመስጠት ማቀዱን አስታውቀዋል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም