አገራዊውን ለውጥ ለማስቀጠል በአስተሳሰብ ግንባታ ላይ ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ ተመለከተ

70
ሶዶ ሰኔ 14/ 2011 በአገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ለማስቀጠል በአስተሳሰብ ግንባታ ላይ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ተመለከተ። የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ከአጋሮቹ ጋር "እኔ ያገባኛል ጥላቻን ነቅዬ ፍቅርን እተክላለሁ" በሚል መሪ ቃል ያዘጋጀው መድረክ ተካሂዷል። ዩኒቨርሲቲው ከያገባናል ፀረ-ኤድስ በጎ አድራጎት ማህበርና ከሻዴይ ኢቨንት ኦርጋናይዜርሽን ጋራ በመተባበር ባዘጋጀው መድረክ የአዕምሮ ማንቂያ፣የአስተሳሰብ ለውጥ፣የአመራር ክህሎትና ሕዝባዊ አደረጃጀት ላይ ያተኮረ ስልጠና ተሰጥቷል። የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት የአመራር ክህሎትን በማሳደግ የለውጥ ኃይሉን መደገፍ ይገባል። ውስን የሀገሪቱን ሀብት በአግባቡ ከመጠቀም ባለፈ ምቹ የሆነ የአሰራር ስርዓትን በመዘርጋት ትውልዱ የሚማርበትን ሁኔታ መፍጠር እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል። አገርን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ለሰው ሀብት አቅም ግንባታ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚያስፈልግ ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል። የያገባናል ፀረ-ኤች አይቪ ኤድስ በጎ አድራጎት ማህበር ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ መስተዋት ስሜ ማህበሩ በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰቱ የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት ከሚመለከታቸውው አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። "በአገሪቱ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ በያገባኛል ስሜት መንቀሳቀስ ተገቢ ነው" ያሉት ሥራ አስኪያጇ፣ የአመለካከትና የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ማህበሩ ድርሻውን እንደሚወጣ አመልክተዋል። በመድረኩ የህይወት ተሞክሮ ያካፈሉት አቶ ዳዊት ድርምስ የተባሉ ግለሰብ  በሰጡት አስተያየት ሰዎች በግል ሕይወታቸው ስኬታማ ለመሆን በእቅድና በዓላማ መመራት እንዳለባቸው ገልጸዋል። እያንዳንዱ ሰው ዕውቀቱን ተጠቅሞ ውጤት ለማምጣት የእችላለሁና የአሸናፊነት መንፈሳዊ ጥንካሬ ማዳበር እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡ በመድረኩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣የሃይማኖት መሪዎች፣የአገር ሽማግሌዎች፣የወጣት አደረጃጀቶችና ተመራቂ ተማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም