አደንዛዥ እጾችና አደገኛ መድኃኒቶች በወጣቶች ስብዕና ግንባታ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደሩ ነው

121
ሰኔ 14/2011 በሀገሪቱ የአደንዛዥ እጾችና አደገኛ መድኃኒቶች ዝውውር በወጣቶችና ታዳጊዎች ስብእና ግንባታ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን የሴቶች፣ ወጣቶችና ሕፃናት ሚኒስቴር አስታወቀ። በአዲስ አበባ ከአሉታዊ መጤ ልማዶችና አደንዛዥ እጽ ነፃ የሆኑ ትምህርት ቤቶችንና አካባቢን መፍጠር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረና  በሚኒስቴሩ የተዘጋጀ የምክክር መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል። በመድረኩ ላይ የተገኙት በሚኒስቴሩ የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ህይወት ኃይሉ እንዳስታወቁት በአሁኑ ወቅት በከተሜነት መስፋፋትና የሀገሪቱን ባህል በሚጋፉ ምክንያት ወጣቶች ለከፋ ችግር እየተጋለጡ ነው። በተለይ የአደንዛዥ እፆችና አደገኛ መድኃኒቶች ዝውውር በወጣቶችና ታዳጊዎች ስብእና ግንባታ ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ እያሳደረ መሆኑን ጠቅሰዋል። "በተለይ በትምህርት ቤቶች የሚውሉ ወጣቶች ከራሳቸው አልፎ ሌሎች ጓደኞቻቸው ላይ በሚፈጥሩት አሉታዊ ተፅእኖ ሃገራቸውን ለመረከብ በቂ ዝግጅት በሚያደርጉበት ወሳኝ እድሜያቸው ላይ ለተለያዩ ሱሶች እየተገለጡ ራዕይ አልባ እየሆኑ ነው" ብለዋል።"በዚህም ምክንያት ወጣቶቹ ከማህበረሰባቸው ባህልና ሞራል ጋር የሚጣረሱ ድርጊቶችን ሲፈጽሙ ይስተዋላሉ ያሉት" ሚኒስትር ዴኤታዋ እንቅስቃሴያቸው በአደንዛዥ ዕፆች ላይ መሰረት ያደረገና ከዛ ውጭ መንቀሳቀስ የማይችሉ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል። ወጣቶችን ከአሉታዊ መጤ ልማዶችና አደንዛዥ እፅ ተጋላጭነት ለመከላከል ሁሉም አካል ሊረባረብ እንደሚገባው አሳስበዋል። ሚኒስቴር መስሪያቤታቸው የሚመለከታቸውን አካላት በማስተባበር በወጣቶችና ታዳጊዎች ስብእና ልማት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ መጤ ባህሎችና አደንዛዥ እፆችን ለመከላከል ሃገራዊ ግብረኃይል በማቋቋምና የስትራቴጂክ እቅድ በማዘጋጀት ወደ ስራ መገባቱን አስታውቀዋል። ይህ መድረክም የእንቅስቃሴው አካል ሲሆን በተለይ በአዲስ አበባ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ዙሪያ የሚሰሩ ባለድርሻ አካላት በወጣቶች ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ተረድተው ችግሩን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ጠንካራ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ታስቦ መድረኩ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል። መድረኩ እያጋጠሙ ባሉ ችግሮችና በተገኙ ልምዶች ላይ በመምከር በቀጣይ የተሻለ ስራ በማከናወን መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ጭምር መዘጋጀቱን ገልጸዋል የትምህርት ተቋማት ከአሉታዊ መጤ ልማዶችና አደንዛዥ እጽ ፅዱና ምቹ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለመምከር ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው በዚሁ መድረክ ላይ ከአዲስ አበባ ከተማ የተውጣጡ መምህራን፣ የትምህርት አመራር አካላትና የወላጅ ተወካዮች ተሳትፈዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም