በዲጋ ወረዳ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የአራት ሰዎች ህይወት አለፈ

49
ነቀምቴ  ሰኔ 14 / 2011 በምስራቅ ወለጋ ዞን በዲጋ ወረዳ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የአራት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በ13 ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን ፖሊስ ገለጸ። የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የትራፊክ ደንህንነት ተቆጣጣሪ ዲቪዚዮን ኃላፊ ኢንስፔክተር ከበደ ኤጄርሶ ለኢዜአ እንዳስታወቁት አደጋው የደረሰው በፊሮምሳ ቀበሌ ልዩ ስሙ ከታ የተባለ ስፍራ ደረሰው ዛሬ ከቀኑ ስምንት ሰዓት አካባቢ ነው። አደጋው የደረሰው ከጊምቢ ወደ ነቀምቴ በሚጓዝ የሰሌዳ ቁጥር ኢት 3-52156 ከፍተኛና ከነቀምቴ ወደ ጊምቢ ይጓዝ በነበረ የሰሌዳ ቁጥር ኦሮ 3-60031መለስተኛ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት መሆኑን አስረድተዋል። የመለስተኛ የሕዝብ ማመላለሻ አሽከርካሪው ከባድ የአካለ ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል እንደሚገኝበትም ኃላፊው ገልጸዋል። በአደጋው ከባድና ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው ተሳፋሪዎች በወለጋ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል የህክምና አገልግሎት እየተሰጣቸው መሆኑን ተናግረዋል። የከፍተኛ የሕዝብ ማመላለሻው አሽከርካሪ በሕግ ቁጥጥር ሥር መዋሉንም ኢንስፔክተር ከበደ አስታውቀዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም