በ2025 ካርቦን ልቀትን ዜሮ ለማድረግ እየሰራሁ ነው - የአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን

76
አዲስ አበባ ሰኔ14/2011 የአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን በ2025 የካርቦን ልቀትን ዜሮ ለማድረስ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ገለጸ። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና አርብቶ አደርና አካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኮሚሽኑ የ2012 በጀት ዓመት ረቂቅ ዕቅድ ላይ ዛሬ ተወያይቷል። ኮሚሽኑ እንዳመለከተው፤ ወደልማት ከመገባቱ በፊት የካርቦን ልቀት በአካባቢ ላይ የሚያደርሰውን ተጽኖ ከግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል። በአገር ዓቀፍ ደረጃ እየተለቀቀ ያለውን 134 ሚሊዮን ቶን የካርቦን ልቀት ለመቀነስ የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት በሁሉም ሴክተሮች የመለካት ስራ ቢካሄድም ወጥ የሆነ አሃዝ እንደሌለ የአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ ገልጸዋል። ይህንን ለማስተካከል ኮሚሽኑ ከሚመለከታቸው የፌዴራልና የክልል ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም ጠቁመዋል። ደን ለማልማት የሚተከለው ችግኝ የማይጸድቅበትን ችግር ለመፍታትና በክልሎች መካከል ያለውን ልዩነት ለማስተካከል እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል። የተቀናጀ የመሬት ፖሊሲና አያያዝ ተግባራዊ በማድረግ የችግኝ መጽደቅ ችግሩን በዘላቂነት መፍታት ያስችላል ሲሉ ጠቁመዋል። ''በዓመቱ 4 ነጥብ 27 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከልና የጽድቀት መጠኑንም 70 በመቶ ለማድረስ ይሰራል ነው'' ያሉት ፕሮፌሰር ፍቃዱ። ችግኝ በዘመቻ ብቻ ከመትከል በተጨማሪ ከተተከሉ በኋላ ተገቢውን እክብካቤ ማድረግ፣ ችግኝ ተተከለበትን ቦታ መከለል፣ ከእንስሳት ንክኪ በመጠበቅ ላይ በትኩረት እንሰራለን ብለዋል። ኮሚሽኑ በ2012 ዓ.ም ከ20 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት፣ ሀይቆች፣ ወንዞችን ከመጤና ወራሪ አረሞች ለመከላከል እቅድ መያዙንም ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል። ኮሚሽኑ በዕቅዱ 2 ነጥብ 75 ሚሊዮን የተሻሻሉ የማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችን የማሰራጨት ስራ ይሰራልም በዚህም ወደ አየር የሚለቀቀውን ጋዝ ለመቆጣጠር እንደሚያግዝ ኮሚሽነሩ ተናግረዋል። የእንጨት ኢንዱስትሪ በ200 ሺህ ቶን ለማሳደግና ወደ 88 ሚሊዮን ቶን አጣና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እቅድ መያዙን ገልጸዋል። የተለያዩ መረጃዎችን በማሰራጨት ህብረተሰቡ በደን ሀብት ዙሪያ ግንዛቤ እንዲያገኝም ይሰራል ብለዋል። ከባለድርሻ አካላት ጋር በለጠ የቅንጅት ስራ በመስራት የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ለማሳከት ዕቅድ መያዙንም ገልጸዋል። በፓርኮች ላይ በደን ላይ የሚከሰተውን የእሳት ቃጣሎ ለመከላከል ከሚመለከተው የመንግስት አካላት ጋር ኮሚሽኑ በቅንጅት እንደሚሰራ ተናግረዋል። ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ ኮሚሽኑ ያቀረበው የመሪ ዕቅድ ሪፖርት ጥሩ መሆኑን ገልጸው ለተፈጻሚነቱ በትኩረት መሰራት እንዳለበት አሳስቧል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም