በዘንድሮው መኸር የተሻለ ለማምረት እየሰራን ነው…የትግራይ ማዕከላዊ ዞን አርሶ አደሮች

62
ሰኔ 14/2011 በዘንድሮው መኸር ምቹ ሁኔታዎችን በመጠቀም ከአምናው የተሻለ ምርት ለማግኘት እየሰሩ መሆናቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የትግራይ ማዕከላዊ ዞን አርሶ አደሮች ገለጹ። በዞኑ እስከ አሁን ከ75 ሺህ 500 ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች መሸፈኑን የዞኑ የእርሻ ማስተባባሪያ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል። አርሶ አደሮቹ እንደገለጹት በዘንድሮው መኸር የሚፈልጓቸው የግብርና ግብዓቶችን ቀደም ብለው በማግኘታቸው የዘር ስራውን ፈጥነው ጀምረዋል። በላዕላይ ማይጨው ወረዳ የሓጸቦ ቀበሌ አርሶ አደር ግዛቸው ለገሰ እንዳሉት በዘንድሮው መኸር የተሻለ ምርት ለመሰብሰብ እንዲያስችላቸው የእርሻ ስራቸውን በትኩረት እያከናወኑ ይገኛሉ። ከቅድመ ዝግጅት ተግባራት ጀምሮ እየጣለ ያለውን በቂ ዝናብ ለመጠቀም ቀድመው ለሚዘሩ ሰብሎች ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አርሶ አደሩ ተናግረዋል። እስከ አሁን አንድ ሄክታር ማሳቸው በተለያዩ ሰብሎች መሸፈናቸውን ቀሪ ማሳቸውን ደግሞ ሶስት ጊዜ በማረስ አለስልሰው ጤፍ ለመዝራት መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል። የማዳበሪና ምርጥ ዘር አቅርቦት ችግር እንዳላጋጠማቸው የተናገሩት አርሶ አደር ግዛቸው የተገኘውን የዝናብ ውሃ ወደ እርሻ ማሳ በማስገባት የግብርና ባለሙያዎች ሊያጋጥም ይችላል ያሏቸውን የውሃ እጥረት የመከላከል ስራ እንደሚያከናውኑም አስረድተዋል። በዓድዋ ገጠር ወረዳ የላዕላይ ሎጎምቲ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ኪዳነ ገሰሰው በበኩላቸው በተሰጣቸው ስልጠና እና በባለሙያዎች በሚደረገው ድጋፍ መሰረት ኩታ ገጠም የእርሻ ሰራዎችን እያከናወኑ እንደሆነ ተናግረዋል። ግማሽ ሄክታር ማሳቸውን በማሸላ መሸፈናቸውን የተናገሩት አርሶ አደሩ በአከባቢያቸው ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ እየጣለ በመሆኑ በቡቃያ ጉዳት እያደረሰ እንደሚገኝ ገልጸዋል። በዞኑ የእርሻ ማስተባባሪያ ጽሕፈት ቤት የስነ-አዝርእት ባለሙያ ተወካይ አቶ ረዳኢ በላይ እንደተናገሩት በዞኑበቂ የዝናብ ስርጭት በመኖሩ ቀድመው ለሚዘሩ ሰብሎች ምቹ ሁኔታን እፈጠረ ነው። “በምርት ዘመኑ ሊሸፈን ከታሰበው 192 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥም እስከ አሁን ከ75 ሺህ 500 በላይ ሄክታር በላይ በበቆሎ፣ ማሸላ፣ ዳጉሳ እና ስንዴ በመሳሰሉ ሰበሎች ተሸፍኗል” ብለዋል። ለምርት ዘመኑ 792 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያና ተመሰሳይ መጠን ያለው ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ መከፋፈሉን ገልጸው በአጠቃላይ እስከ አሁን ከ21 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያና 250 ኩንታል ምርጥ ዘር ጥቅም መዋሉን ጠቁመዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም