የደቡብ ወሎ ዞን ባለሀብቶች ወደ ማምረት እንዲሸጋገሩ ችግሮች እንዲፈቱላቸው ጠየቁ

52
ደሴ ሰኔ 14 /2011 በደቡብ ወሎ ዞን በኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሀብቶች ግንባታቸውን አጠናቀው ወደ ማምረት እንዲሸጋገሩ ችግሮች እንዲፈቱላቸው ጠየቁ፡፡ ባለድርሻዎችን ያካተተ ውይይት በኮምቦልቻ ከተማ እየተካሄደ ነው። በዞኑ በተለያዩ ዘርፎች የኢንቨስትመንት ቦታ የወሰዱ ባለሀብቶች ወደ ምርት ለመግባት እየተገጠሟቸው ያሉት ችግሮች እንዲፈቱላቸው ጠይቀዋል። በኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሀብቶች  መካከል  አቶ መሐመድ ሐሰን የከረሜላና ጣፋጭ ምግቦች ፋብሪካ ለመክፈት በ2009 መጨረሻ በኮምፖልቻ ከተማ ግማሽ ሄክታር መሬት መቀበላቸውን ተናግረዋል። ከስድስት ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ግንባታውን በ15 ሚሊዮን ብር ወጪ ለማጠናቀቅ ታቅዶ እንደነበር ያስታወሱት ባለሀብቱ፣ መሠረተ ልማት ባለመሟላቱ ግንባታውን ለማካሄድ መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡ የአማህተመ መኪናና ሼድ ማምረቻ ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ አቶ ታምራት ሞላ በበኩላቸው በአንድ ቢሊዮን ብር ወጪ ፋብሪካውን በሁለት ዓመታት ውስጥ ለመገንባት በ2008 መሬት መውሰዳቸውን አስታውሰዋል፡፡ ለቦታው የመሠረተ ልማት ተቋማት ስላልተሟሉ ግንባታውን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እንደተቸገሩ ተናግረዋል። የፋብሪካ ግንባታው ከ75 በመቶ በላይ መጠናቀቁን የገለጹት ባለሀብቱ ፋብሪካው ሲጠናቀቅ በዓመት ከ150 በላይ ተሽከርካሪዎችን የመገጣጠምና ከ50 በላይ ሼዶችን አምርቶ የመገጣጠም አቅም እንደሚኖረው አመልክተዋል። ፋብሪካው ሲጠናቀቅ ከ500 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ ሥራ እንደሚፈጥር ጠቁመዋል። የደቡብ ወሎ ዞን ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ሱምያ ደሳለው በባለሀብቶች የሚነሱ ችግሮችን ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። በራሳቸው ችግር ወደ ግንባታ ባልገቡ ባለሀብቶች ላይ በቀጣይ እርምጃ እንደሚወሰድም ተናግረዋል።እስካሁንም በ19 ባለሀብቶች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን አስታውቀዋል። የአማራ ክልል ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ መላኩ አለበል መንግሥት የባለሀብቶቹን ችግሮችን በጥናት በመለየት የመፍትሄ አቅጣጫ እንደሚቀመጥ ተናግረዋል። በዞኑ ከ54 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ከ800 በላይ ባለሀብቶች ለኢንቨስትመንት ቦታ ወስደዋል። ከነዚህም መሬት ከወሰዱ ባለሀብቶች ውስጥ 200 የሚሆኑ ባለሀብቶች ብቻ ግንባታቸውን አጠናቀው ወደ ምርት መግባታቸው ተገልጿል። .በውይይቱ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ባለሀብቶች ተሳትፈዋል፡፡በውይይቱ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ባለሀብቶች ተሳትፈዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም