በምስራቅ ጎጃም ዞን አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከትን ለመከላከል እየተሰራ ነው

135
ሰኔ 14/2011 በምስራቅ ጎጃም ዞን አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በሽታን ለመከላከል የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን የዞኑ ጤና መምሪያ አስታወቀ። የመምሪያው ኃላፊ አቶ ጌታነህ ድረስ ለኤዜአ እንደገለጹት ከክረምቱ መግባት ጋር ተያይዞ የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት ወረርሽኝ በሽታ እንዳይከሰት በየወረዳው የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው። ለችግሩ መንስኤ ሊሆኑ ይችላሉ በተባሉ የፀበል ቦታዎች፣ ትምህርት ቤቶችንና የኢንቨስትመንት ቦታዎችን በመለየት የተለየ ጥንቃቄ እንዲደረግ ትኩረት መደረጉንም ተናግረዋል፡፡ "በተልይም በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች በሽታው በመታየቱ በማንኛውም መንገድ ሊሸጋገር ስለሚችል 40 ሺህ ለሚሆኑ አንድ ለአምስት የጤና አደረጃጀቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ተሰጥቷል" ብለዋል። ድንገት በሽታው ቢከሰት ፈጥኖ ህክምናውን ለመስጠት እንዲቻልም በጤና ጣቢያዎችና በሆስፒታሎች የህክምና ማዕከላትን የመለየትና የማደራጀት ስራ እየተሰራ እንደሚገኝም አቶ ጌታነህ ገልፀዋል፡፡ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ ቢሆንም ለውሃ ማከሚያ የሚያገለግል ውሃ አጋርና ለህሙማን በፈሳሽ መልክ የሚሰጥ ኦ.አር.ኤስ እጥረት በማጋጠሙ ለክልሉ ጤና ቢሮ ጥያቄው መቅረቡን አስታውቀዋል፡፡ በማንኛውም መንገድ የአተት ወረርሽ በሽታ ሊከሰት ስለሚችል ህብረተሰቡ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባም አሳስበዋል ። "በተለይም የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በሽታን ለመከላከልም ህብረተሰቡ ውሃን አፍልቶና አቀዝቅዞ በመጠጣት፣ አትክልቶችን አብስሎ በመመገብና የግልና የአካባቢን ንፅህና በመጠበቅ እራሱን  ከበሽታው ሊጠብቅ ይገባል" ብለዋል፡፡ የበሽታው ምልክት እንደታየም ለጤና ባለሙያዎች ማሳወቅና ፈጥኖ ወደ ህክምና ተቋም መውሰድ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ በደብረ ማርቆስ ከተማ የአርሴማ ጸበልተኛ ወይዘሮ መልስሽ ይስማው በሰጡት አስተያየት በፀበል ቦታው የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በሽታ በሚከሰትበት መንገድና በመከላከል አማራጮች ዙሪያ  ግንዛቤ ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ ባገኙት ትምህርት መሰረትም ከሽንት ቤት መልስ እጃቸውን በሳሙና በመታጠብና መሰል ጥንቃቄዎችን እያደረጉ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ የአነደድ ወረዳ የወቢ እነችፎ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ምንይሻው ዳኘ በበኩላቸው በሽታው በእርሳቸውም ሆነ በቤተሰቦቻቸው ላይ እንዳይከሰት የግልና የአካባቢ ንጽህናቸውን በመጠበቅ ጥንቃቄ እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በዞኑ ባለፈው ዓመት ተከስቶ በነበረው አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በሽታ ከ50 በላይ ሰዎች ታመው በተደረገላቸው ሕክምና መዳናቸውን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል ።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም