የውሃ ሀብት አጠቃቀምን ለማዘመን በሚደረገው ጥረት ዩኒቨርሲቲዎች የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል…ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ

195
አርባ ምንጭ ሰኔ 2/2010 የውሃ ሀብት አጠቃቀምን ለማዘመን በሚደረገው እንቅስቃሴ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው የኢፌድሪ ውሃ፣ መስኖና ኤለክትሪክ ሚኒስትሩ አሳሰቡ ፡፡ 18ኛው ዓለም አቀፍ ዘላቂ የውሃ ልማት አውደ ጥናት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሲጀመር ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ እንደገለጹት በአገሪቱ የውሃ ሐብት አጠቃቀም ላይ በቂ ጥናትና ምርምር አልተደረገም። ኢትዮጵያ 123 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የገጸ ምድርና 36 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የከርሰ ምድር የውሃ ሀብት ቢኖራትም አገሪቱ ተገቢ ጥቅም አለማግኘቷን ገልጸዋል። የውሃ ሀብት አጠቃቀምን ለማዘመን መንግስት በሚያደርገው እንቅስቃሴ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በምርምር የተደገፈ ሥራ በመስራት ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የውሃ ሃብትን በበቂ ሁኔታ ጥቅም ላይ ለማዋል በተደረገው እንቅስቃሴ በንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት የተሻለ ተግባር ቢከናወንም  በመስኖ ልማት ሰፊ ክፍተት መኖሩን ሚኒስትሩ አመልክተዋል ፡፡ “በቀሪ የዕቅድ ዘመን ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ የግብርና ምርቶችን በስፋት ለማምረት ህዝቡን ማዕከል ያደረጉ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሥራዎች በዘርፉ ይከናወናሉ” ብለዋል ፡፡ በእዚህም በተለይ ድርቅ ባለባቸው አካባቢዎችም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የውሃ ልማት አቅርቦት እንዲኖር በተለየ መልኩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡ “በ2017 ዓ.ም የውሃ አቅርቦትን በገጠርና በከተማ ሙሉ በሙሉ ለማዳረስ እየተሠራ ነው” ያሉት ሚኒስትሩ፣ በጥናትና ምርምር የተገኙ ዕውቀቶችን ወደተግባር በመለወጥ በኩል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የጎላ ሚና መጫወት አለባቸው” ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዳምጠው ዳርዛ በበኩላቸው ዘላቂ የውሃ ልማትን ለማረጋገጥ በሚሰራው ስራ ዩኒቨርሲቲው ላለፉት 30 ዓመታት በመማር ማስተማር፣ በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት  የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡ ተቋሙ በምስራቅ አፍሪካ የውሃ ልህቀት ማዕከል ሆኖ ለማገልገል ግብ ይዞ እየሰራ መሆኑን ገልፀው፣ ዘንድሮ ምርምር ብቻ የሚያካሂድ የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስትቲዩት ማዕከል ራሱን ችሎ እንዲቋቋም ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ ማዕከሉን በቤተሙከራ ዕቃዎች ከማጠናከር ባሻገር በዘርፉ የድህረ ምረቃ ትምህርት መጀመሩን ጠቅሰዋል ፡፡ በአውደ ጥናቱ ላይ በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ተመራማሪዎችና ውሳኔ ሰጪ አካላት መገኘታቸው በአገሪቱ ዘላቂ የውሃ ልማትን ለማረጋገጥ ዓይነተኛ ፋይዳ እንዳለውም ጠቅሰዋል ፡፡ አገሪቱ 45 ሺህ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ከውሃ የማመንጨት አቅም ቢኖራትም እስከዛሬ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው 4ሺህ 300 ሜጋ ዋት ብቻ መሆኑን የጠቀሱት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የሳይንትፊክ ዳይሬክተር ዶክተር ኢንጂነር አብደላ ከማል ናቸው ፡፡ በአውደ ጥናቱ ላይ በዘርፉ የተከናወኑ 22 ጥናታዊ ጽሑፎች እንደሚቀርቡ ጠቁመው ጥናቶቹን በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ወደ ተግባር በመቀየር የአገሪቱን የውሃ ሀብት አሁን ካለበት ደረጃ ከፍ ለማድረግ እንደሚሰራ አስታውቀዋል። በአገሪቱ 5 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ የሚለማው የገጸ ምድርና የከርሰ ምድር የመስኖ ውሃ አቅርቦት የግብርና ዘርፉን ለመደገፍ እንደሚያስችልም ጠቁመዋል፡፡ ለሁለት ቀናት እየተካሄደ ባለው አውደ ጥናት የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩን ጨምሮ የተለያዩ ውሳኔ ሰጪ አካላት እንዲሁም የአገር ውስጥና የውጭ ተመራማሪዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም