በጉጂ ዞን ከ143 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለዘር ተዘጋጅቷል

81
ነገሌ ሰኔ 13/2011  በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ለመኽር አዝመራ ከ143 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሁለት ዙር ታርሶ ለዘር መዘጋጀቱን የዞኑ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡ የዞኑ አርሶ አደሮችም በቀጣዩ ወር አጋማሽ ለሚጀምሩት የመኽር እርሻ የምርት ማሳደጊያ ወቅቱን ጠብቆ እንዲቀርብላቸው ጠይቀዋል። በጽህፈት ቤቱ የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ቦነያ ሁቃ እንዳሉት በዚህ ዓመት የመኽር አዝመራ ከ160 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ይሸፈናል፤ እስካሁንም ከ143 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለሁለተኛ ጊዜ ታርሶ ለዘር ተዘጋጅቷል፡፡ በገብስ፣ ባቄላ፣ ስንዴ፣ ጤፍና በቆሎ ሰብሎች በዋናነት በዘር ከሚሸፈነው ከዚህ መሬት ከ3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል። በዚህ ዓመት በዘር የሚሸፈነው መሬት ካለፈው ዓመት በ5 ሺህ  ሄክታር የሚበልጥ ሲሆን ለመሰብሰብ የታቀደው ምርትም በ120 ሺህ ኩንታል ብልጫ እንደሚኖረው አመልክተዋል፡፡ ባለሙያው እንዳሉት ምርታማነትን ለማሳደግ ለዞኑ የመኽር አዝመራ ከታቀደው 58 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ እስካሁን 38 ሺህ ኩንታሉ ለአርሶ አደሩ ቀርቧል፡፡ በማሳ ዝግጅት፣ በግብአት አጠቃቀም፣ በእንክብካቤ ጥበቃና በምርት አሰባሰብ ለአርሶ አደሩ የማነቃቂያ ስልጠና በባለሙያዎች እየተሰጠ መሆኑንም ነው የገለጹት። ባለፈው ዓመት በዝናብ እጥረት ያጡትን የመኽር አዝመራ ዘንድሮ ለማካካስ መሬታቸውን ደጋግሞ በማረስ የማሳ ዝግጅት ማድረጋቸውን የገለጹት ደግሞ በዞኑ አናሶራ ወረዳ የሶሎሎ ቆቦ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አበራ ዴገና ናቸው፡ በጤፍና ስንዴ ዘር ለመሸፈን ለመኽር አዝመራ ላዘጋጁት 4 ሄክታር መሬት 4 ኩንታል ማዳበሪያ እንደሚያስፈልጋቸው ጠቁመዋል፡፡ የምርት ማሳደጊያው በወቅቱ እንዲቀርብ እሳቸውና የአካባቢያቸው ነዋሪዎች ለሚመለከተው አካል ተደጋጋ ጥያቄ በማቅረብ በቅርቡ አዎንታዊ ምላሽ እንዳገኙ ገልጸዋል፡፡ ባለፈው ዓመት የምርት ማሳደጊያ ወቅቱን ጠብቆ ባለመቅረቡ የአዝመራ ወቅት እንዳለፈባቸው የተናገሩት ድግሞ በዞኑ አናሶራ ወረዳ ገለቾ ገዳባ ቀበሌ የሚኖሩት አቶ ዋቴ ሺንቃ ናቸው። ዘንድሮ ተመሳሳይ ችግር እንዳይከሰት የአዝመራ ወቅት ከመጀመሩ አስቀድሞ የምርት ማሳደጊያ እንዲቀርብላቸው ጠይቀዋል፡፡ "በግብአት አጥረት፣ በአየር ነብረት ለወጥና በዝናብ እጥረት ባለፈው ዓመት የቀነሰብኝን ምርት ለማካካስ በዚህ ዓመት 3 ሄክታር መሬት ደጋግሜ በማረስ አዘጋጅቺያለሁ" ብለዋል፡፡ በባቄላና በስንዴ ዘር ለመሸፈን ደጋግመው በማረስ ለመኽር አዝመራ ላዘጋጁት 3 ሄክታር መሬት 3 ኩንታል ማዳበሪያ እንደሚፈልጉም ጠቁመዋል፡፡ በጉጂ ዞን ከሐምሌ አጋማሽ እስከ መስከረም አጋማሽ የመኽር አዝመራ ወቅት መሆኑ ከጽህፈት ቤቱ የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም