በአካባቢው ተፈጥሮ የነበረው ግጭትና አለመግባባት በእርቅና ይቅርታ መፈታቱ አስደስቶናል--- የሸኮ ወረዳ ነዋሪዎች

76
ሰኔ 14/2011 በአካባቢው ተፈጥሮ የነበረው ግጭትና አለመግባባት በእርቅና ይቅርታ መፈታቱ እንዳስደሰታቸው በቤንች ሸኮ ዞን የሸኮ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ ከወረዳው ነዋሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት ቄስ ወንድሙ ጃርካ እንድተናገሩት ባለፉት ወራት በአካባቢው ተከስቶ የነበረው የሠላም መደፍረስ ህብረተሰቡን ስጋት ላይ ጥሎ እንደነበር አስታውሰዋል። መንግስት ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በመቀናጀት ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት በእርቅና በይቅርታ እንዲፈታ እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታና ተገቢ መሆኑንም ጠቁመዋል። "እርቅና ይቅርታ ያለፈውን በመተው መጪውን ጊዜ የተሻለ ማድረግ ነው" ያሉት ቄስ ወንድሙ ሁሉም ያለፈውን መጥፎ ክስተት በመተው ከልብ ይቅር መባባል እንዳለበት መክረዋል። አቶ ዳዊት ዳንኤል የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው የአካባቢው ሰላም አስተማማኝና ዘላቂ መፍትሄ የሚያገኘው የተጋጩ አካላት ይቅር ሲባባሉና ወደ ቀደመ አንድነታቸው ሲመለሱ መሆኑን አስረድተዋል። "መንግስት እርቅና ይቅርታን እንደመፍትሄ መውሰዱ የተሻለ አማራጭ በመሆኑ ሁላችንንም አስደስቶናል" ብለዋል፡፡ የሠላም ዋጋ በምንም ነገር ሊተካ እንደማይችል የገለጹት ነዋሪው ባለፉት ወራት በአካባቢው ተከስቶ የነበረው የሰላም መደፍረስ የልማት ስራቸውን እንዳይሰሩ እንቅፋት ሆኖባቸው መቆየቱን አስታውሰዋል። ሰላም በመንግስትና በጸጥታ አካላት ብቻ የሚረጋገጥ እንዳልሆነ የጠቆሙት አቶ ዳዊት የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አቶ አማን አቶሳ የተባሉ አስተያየት ሰጭ በበኩላቸው ለዘመናት የዘለቀው የአብሮነትና የአንድነት ባህል እንዳይሸረሸር ልዩነቶች ሲኖሩና አለመግባባቶች ሲፈጠሩ በውይይይትና በምክክር መፍታት እንደሚገባ ታናግረዋል። "ለአካባቢያችን ሠላም ሁላችንም ዘብ መቆም አለብን" ያሉት አቶ አማን እሳቸውም እንደ አንድ የአካባቢው ነዋሪ ለሰላም ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል። በአካባቢው ተከስቶ በነበረው ግጭት ቅራኔ ውስጥ ገብተው የነበሩ አካላት ወደላምና እርቅ እንዲመጡ በመደረጉ ደስተኛ መሆናቸውንም ተናግረዋል። በአካባቢው ተከስቶ የነበረውን የሰላም መደፍረስ ተከትሎ በሸኮ ከተማ የእርቅና የሰላም ኮንፍረንስ መካሄዱ የሚታወስ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም