የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 28ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከቅዳሜ እስከ ሰኞ ይደረጋሉ

78
ሰኔ 14/2011 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 28ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከቅዳሜ እስከ ሰኞ በአዲስ አበባና በክልል ስታዲየሞች ይደረጋሉ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ግንቦት 23 ቀን 2011 ዓም ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ በየጨዋታው የሚታየውን ችግር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተነጋግሮ ዘላቂ መፍትሄ እስኪመጣ ድረስ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቋረጥ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል። በመሆኑም ፌዴሬሽኑ የተቋረጠር የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ እንዲካሄድ በመወሰኑ በዚህ ሳምንት የመጨረሻ ቀናት ጨዋታዎቹ ቀጥለው ይካሄዳሉ። በዚህም በ28ኛ ሳምንት የሊጉ መርሃ ግብር ጨዋታዎች በተያዘላቸው ፕሮግራም መሰረት ከነገ ጀምሮ ሲካሄዱ ባህርዳር ከተማ ከወላይታ ድቻ፣ ስሁል ሽረ ከደደቢት፣ ሃዋሳ ከተማ ከመከላከያ እንዲሁም ጅማ አባጅፋር ከኢትዮጵያ ቡና ነገ በ9:00 ሰዓት በክልል ስታዲየሞች ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። መቐለ 70 እንደርታ ከደቡብ ፖሊስ፣ አዳማ ከተማ ከፋሲል ከተማ እና ሲዳማ ቡና ከድሬዳዋ ከተማ እሁድ በተመሳሳይ 9:00 ሰዓት በክልል ስታዲየሞች የሚደረጉ ጨዋታዎች ናቸው። ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ሰኞ ሰኔ 17 ቀን 2011 ዓ.ም በ11:00 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ። ፕሪሚየር ሊጉን ፋሲል ከተማ በ52 ነጥብ ሲመራ መቐለ 70 እንደርታ በ50 ነጥብ ሁለተኛ፣ ሲዳማ ቡና ደግሞ በ49 ነጥብ ሶስተኛ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ46 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ይዘው ይከተላሉ። ደቡብ ፖሊስ፣ ስሁል ሽረ እና ደደቢት ደግሞ በሊጉ ግርጌ ላይ ተቀምጠው በወራጅ ቀጠና ስጋት ወስጥ ይገኛሉ። ኮከብ ግብ አግቢነቱን የመቐለ 70 እንደርታው አማኑኤል ገብረሚካኤልና የሲዳማ ቡናው አዲስ ግደይ በእኩል 15 ጎሎች ሲመሩ ሙጂብ ቃሲም ከፋሲል ከነማ በ14 ጎሎች እንዲሁም ሄኖክ አየለ ከደቡብ ፖሊስ በ12 ጎሎች ሶስተኛና አራተኛ ሆነው ይከተላሉ። የ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 30ኛ ሳምንት ድረስ ያሉ ጨዋታዎች በሙሉ ተደርገው እስከ ሰኔ 30 ቀን 2011ዓ.ም ድረስ የሚጠናቀቁ ይሆናሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም