ኢትዮጵያና ኬንያ ረጅም ዓመት ያስቆጠረውን ትብብራቸውን ለማጠናከር እየሰሩ ነው

61
ሰኔ 14/2011 በናይሮቢ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከናይሮቢ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የሁለቱን አገሮች የ55 ዓመት ትብብር የሚያሳይ የሁለት ቀን ዝግጅት በሚቀጥለው ሳምንት ያካሂዳል። በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር መለስ አለም ባለፈው ረቡዕ በጽህፈትቤታቸው በሰጡት መግለጫ "ኢትዮጵያ በቀጠናው ሰላምን መሰረት ያደረገ ዲፕሎማሲ እንደምትከተል" አስረድተዋል። “የኢትዮ-ኬንያ የሁለትዮሽ ግንኙነት በከፍተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፤ አገሮቹ በቀጠናው ሰላምና ደህንነት ጉዳይ በኢጋድ በኩል ከፍ ያለ ሚና አላቸው" ብለዋል “በአንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን የአገሮቹ ግንኙነት እየተበላሸ ነው የሚል የተሳሳተ ዘገባ እመለከታለሁ ይህ ደግሞ መሰረተ ቢስ ወሬ ነው" በማለት ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር ሰላማዊና ጠንካራ ግንኙነት ያላት መሆኑን አስረድተዋል። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና ብሄራዊ የደህንነት ስትራቴጂም ሰላምና የጋራ ትብብርን መሰረት ያደረገ መሆኑን ነው ያብራሩት። ኢትዮጵያ ከኬኒያ ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትም በጋራ መተማመን ላይ የተመሰረተ መሆኑን ተናግረዋል። በኬንያ የሚታተመው ስታር ጋዜጣ ባለፈው ግንቦት 15 የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሞሃመድ ፎርማጆ ኢትዮጵያና ኤርትራ ከአሚሶም ተልዕኮ ውጭ ወደ ሶማሊያ እንዲገቡ መጠየቃቸውን መዘገቡ ይታወሳል። አምደባሳደር መለስ ዘገባውን ” መሰረተቢስነው” በማለት አጣጥለው የአዲስ አበባ እና ናይሮቢ ግንኙነት ለኬንያና ሶማሊያ የዲፕሎማሲ ግንኙነት አጋዥ መሆኑንም ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ወደብ አልባ መሆኗን ተከትሎ ያፈረሰችውን የባህር ሃይል መልሳ ለማቋቋም የምታደርገው ጥረት በኪስማዩ ወደብ ለመጠቀም በማሰብ መሆኑንም ጋዜጣው ጨምሮ ጽፏል። ሰኔ 19 በሚከናወነው ዝግጅት ላይ የሁለቱን አገሮችየ 55 አመት ትብብር አስመልክቶ "ውድድርን መሰረት ያደረገ አጋርነት መመስረት" በሚል ርዕስ የፓናል ውይይት እንደሚደረግም ተገልጿል። በናይሮቢ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ዲፓርትመንት ከፍተኛ ሌክቸረር የሆኑት ዶክተር ጆይ ኪሩ ውይይቱ የአለፉትን አመታት ወደ ኋላ ተመልሶ በመቃኘት የወደፊቱን አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያግዛል ብለዋል። አገሮቹ ያላቸውን የጋራ የልማት ጉጉት በማቀናጀት ኢኮኖሚያቸውን እንዴት ማሳደግ እንደሚችሉም የመከርበታል ብለዋል። አምባሳደር መለስ በበኩላቸው ዝግጅቱ በአገሮቹ መንግስታት መካከል ያለውን ጠንካራ ትብብር ወደ ህዝቡ በማውረድ ለመስራት ያግዛል ብለዋል። በዝግጅቱ የሁለተኛ ቀን ውሎ ቀጣይነት ያለውና የተረጋጋ የፖለቲካ ግንኙነት ለመመስረት የሚረዳ የንግድ ውይይት እንደሚደረግም ይጠበቃል። በመጨረሻም አምባሳደር መለስ “ኢትዮጵያ በሯን ለኬንያ የንግድ ሰዎች ክፍት ማድረጓንና ከዚህ በላይ የንግድ ዲፕሎማሲውን ለማሳደግ ትሰራለች” ብለዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የኬንያ አቻቸውን ሞኒካ ጁማንን በትናንትናው እለት በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው መነጋገራቸው ይታወቃል። የህዝብ ለህዝብ ግንኙነታቸውን ማጠናከርና ማሳደግ በሚያስችለው የተማሪዎች ልውውጥ ላይ በትኩረት መንቀሳቀስ በውይይታቸው ከተዳሰሱ ጉዳዮች መካከል ነው። ኢትዮጵያና ኬንያ ቀደም ሲል በቀጣናው፣ በአፍሪካኅብረት፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅትና በዓለም አቀፍ መድረኮች ያሏቸውን የጋራ ስራዎች ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። ኢትዮጵያና ኬኒያ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር 1954 በቆንስላ ደረጃ መደበኛ የዲፕሎማሲ ግንኙነት እንደጀመሩ መረጃዎች ያመለክታሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም