የሩሲያ የባቡር ኩባንያ በኢትዮጵያና ናይጄሪያ የመስራት ፍላጎት እንዳለው አስታወቀ

174

ሰኔ 14/2011የሩሲያው መንግስታዊ የባቡር ሃዲድ ኩባንያ በአፍሪካ መዳረሻውን በማስፋፋት በኢትየጵያና ናይጀሪያ መዋለ ንዋይ ማፍሰስ እንደሚፈልግ የኩባንያው ተቀዳሚ ምክትል ዳይሬክተር አሌክሳንደር ሚሻሪን መናገራቸውን ዩአርዲዩ ፖይንት ዶት ኮም በገፁ አስነበበ፡፡

ኢትዮጵያ እና ናይጄሪያን ጨምሮ ኩባንያው በአፍሪካ ተደራሽ የመሆን ውጥን እንዳለው ምክትል ዳይሬክተሩ አክለዋል፡፡ በዚህ ወር በሴንት ፒተርስበርግ በተካሄደው ኤስ ፒ አይ ኢ ኤፍ የኢኮኖሚክ ፎረም ላይ ኩባንያው በአፍሪካ ተደራሽነቱን የማስፋት ዕቅድ እንዳለው ዘገባው አስፍሯል፡፡ በፕሮጀክቱም ሁለት ሃገራት ማለትም ጋናና ግብፅ ዋነኛ አጋሮች እንደሆኑ አሌክሳንደር ሚሻሪን ገልፀዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በአጠቃላይ በአፍሪካ ስላለው ሁኔታ የበለጠ ግንዛቤ እንደሚፈልግ ዘገባው አመላክቷል፡፡ እኛ ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች በመጠቀም በግብፅ፣ ጋና፣ ናይጄሪያና በኢትዮጵያ እንሰራልን በማለት በሞስኮ በተካሄደው የሩሲያ-አፍሪካ ኮንፈረንስ ወቅት የኩባንያው ተቀዳሚ ምክትል ዳሬክተር አሌክሳንደር ሚሻሪን መግለፃቸውን ዘገባው ያሳያል፡፡ ኩባንያው ባሳለፍነው ህዳር ወር በግብፅ ካይሮ በተካሄደው የአፍሪካ የገቢና-ወጪ ባንክ ግንዛቤ ማስታወሻ ወቅት በባቡር ሃዲድ ፕሮጀክት ግንባታ ዘርፍ ለመሰማራት መስማማቱን ዩአርዲዩ ፖይንት ዶት ኮም ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም